ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩክሬን ጦርነት፡ በአፍሪካ የስንዴ እጥረት ሊከሰት እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት አስጠነቀቀ
በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ምክንያት በአፍሪካ የስንዴ እጥረት ሊከሰት እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት አስጠነቀቀ።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሩዝ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገው ጦርነት በዓለም አቀፍ ደረጃ "የረሃብ ወጀብ" እና የምግብ ዋስትና እጦት ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
በርካታ የአፍሪካ አገራት እና ድሃ አገራት በሩሲያ እና በዩክሬን የስንዴ ምርት ላይ ጥገኛ መሆናቸውን የገለፁት ዋና ፀሐፊው አሁን ግን በጦርነቱ ምክንያት ስጋት ውስጥ ወድቀዋል ብለዋል።
ከእነዚህ አገራት መካከል ቀድሞውኑም ሕዝባቸውን ለመመገብ የሚታገሉት ቡርኪና ፋሶ፣ ሶማሊያ እና የመን ይገኙበታል።
በመሆኑም ዋና ፀሐፊው ጉቴሬዝ የዓለም የምግብ አቅርቦት ሥርዓትን ከመንኮታኮት ለመታደግ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ዋና ፀሐፊው አክለውም በጦርነቱ ሳቢያ ረሃብ፣ የውሃና የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እየገጠማቸው ላሉ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን ለመርዳት 40 ሚሊየን ዶላር እርዳታ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በድርቅ እየተፈተነች ያለችው ሶማሊያ ለከፋ የምግብ እና የውሃ እጥረት ለተጋለጡ 6.9 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎቿን ለመመገብ ዓለም አቀፍ እርዳታን ጠይቃለች።
የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሃመድ ሁሴን ሮብሌ በሰጡት መግለጫ በአገሪቷ ያለው አስከፊ ሁኔታ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሰዎች ምግብ እና ውሃ ፍለጋ ቀያቸውን ለቀው እንዲወጡ አስገድዷቸዋል። አስቸኳይ እርዳታ ካላገኙም በርካቶች ሊሞቱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
"በሶማሊያ ያለው ድርቅ አፋጣኝ እርምጃ እና አፋጣኝ ሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብን ይጠይቃል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቷ እአአ ከ2011 ወዲህ አስከፊ ድርቅ እያስተናገደች ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእርዳታ ጥሪውን ያቀረቡት የአገሪቷ መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ በረሃብ ሳቢያ ሦስት ሰዎች መሞታቸውን ከዘገበ ከሰዓታት በኋላ ነው። በአካባቢው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ እና እገዳም በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሁኔታውን የባሰ አድርጎባቸዋል።
የአል ሻባብ ታጣቂዎች በደቡብ ምዕራብ በሚገኙና በቁጥጥራቸው ሥር ባሉ አካባቢዎች ምግብና ውሃ ለማከፋፈል በአካባቢው ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ እየተጠቀሙበት ነው።
በሶማሊያ በተከሰተው ከባድ ድርቅ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ መገደዳቸው ተነግሯል።
ባለፈው ዓመት የተባበሩት መንግሥታት በሶማሊያ የተከሰተው ድርቅ እየተባባሰ በመምጣቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፋ ረሃብ እንደተጋለጡ አስጠንቅቆ ነበር።
በኬንያ ፣ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ወደ 13 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ለምግብና ውሃ እጥረት መጋለጣቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።