ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አምስተርዳም በሚገኝ የአፕል መደብር ውስጥ እገታ መፈፀሙን ፖሊስ ገለጸ
አምስተርዳም በሚገኝ አንድ የአፕል ምርቶች መሸጫ መደብር ውስጥ ያጋጠመውን የአጋች ታጋች ድራማ መፍትሄ ለመፈለግ ፖሊስ በአካባቢው ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑ ተዘግቧል።
ማክሰኞ ከሰዓቱን በአምስተርዳም በጦር መሣሪያ የታገዘ ዝርፊያ ሊፈጸም እንደሆነ የሚገልጽ ጥቆማ ፖሊሶች ደርሷቸው በቦታው ሲደርሱ ሁኔታው ወዲያው በውስጥ የነበሩ ሰዎችን ወደማገት ተቀይሯል።
በመሰል ክስተቶች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የፖሊስ አባላት መሣሪያ ከታጠቀው ግለሰብ ጋር ንግግር እያደረጉ ሲሆን በርካታ ሰዎች ደግሞ ከአፕል ምርቶች መሸጫው መደብር አምልጠው እየወጡ ነው።
ነገር ግን ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባትና የደኅንነት ችግር እንዳይፈጠር ሲባል ፖሊሶች ከዚህ በላይ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በመደብሩ ውስጥ ታግተው የሚገኙ ሰዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል የአካባቢው ነዋሪዎች ስለሁኔታው ምስሎችን ከማጋራት እንዲቆጠቡና በማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩል በቀጥታ ማስተላለፋቸውን እንዲተዉ ፖሊስ አሳስቧል።
በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በስፋት እየታዩ ባሉ ምስሎች መሠረት አጋቹ ግለሰብ በአንድ እጁ መሣሪያ በሌላ እጁ ደግሞ አንድን ግለሰብ ይዞ ተስተውሏል።
ምንም እንኳን ኤቲ5 የተባለው የአካባቢው የዜና ምንጭ አንዳንድ የዓይን እማኞች የተኩስ ድምጽ ስለመስማታቸው ቢዘግብም ፖሊስ ግን በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት አስተያየት አልሰጠም።
በርካታ የፖሊስ አባላት በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው የሚገኙ ሲሆን በአሥርታት የሚቆጠሩ ልዩ የፖሊስ አባላትም ሱቁ የሚገኝበት ህንጻ ላይ ከበባ አድርገው እየጠበቁ ነው።
የአካባቢው ነዋሪዎችም ለደኅንነታቸው ሲባል ከህንጻው እንዲርቁ ተደርጓል።
በአምስተደርዳም ታዋቂ ከሆኑ ሱቆች መካከል አንዱ የሆነው ይህ የአፕል መደብር የሚገኘው በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በተገነባው ህንጻ ላይ ነው።