ኮቪድ፡ አውስትራሊያ ድንበሯን ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች በድጋሚ ከፈተች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አውስትራሊያ ወደ ሁለት ዓመት ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ድንበሯን ከፈተች። ይህም ለዓመታት ተለያይተው የቆዩ ቤተሰቦች እንዲገናኙ እና ለቱሪዝሙም ዘርፍም ዕድገት ለማምጣት ያስችላል ተብሏል።
አገሪቱ በኮቪድ ምክንያት ድንበሯን ዘግታ አንዳንድ ጥብቅ የጉዞ እገዳዎችን የጣለችው በፈረንጆቹ የካቲት 2020 ነበር።
በዚህም አውስትራሊያውያን እና አንዳንድ ግለሰቦች ከወራት በፊት ጀምሮ ወደ አገሪቷ እንዲገቡ ቢፈቀድላቸውም አብዛኛዎቹ የውጭ ዜጎች ታግደው ቆይተዋል።
እገዳው መነሳቱን ተከትሎ ሰኞ ዕለት በሲድኒ አየር ማረፊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእንባ ተሞልተው ሲገናኙ ታይተዋል።
ሻርሎት የተባለች ወጣት እንባዋን መቆጣጠር እያቃታት አያቷን ስታቅፋቸው ታይታለች። ናይን ኔትዎርክ ለተባለው መገናኛ ብዙኃንም "በጣም ናፍቆኝ ነበር። ይህን ጉዞ ለረዥም ጊዜ በጉጉት ስጠብቀው ነበር" ብላለች።
አሁን ወደ አገሪቷ ለመግባት ሁለቱን ክትባት የወሰዱ ጎብኚዎች ራሳቸውን ማግለል አይጠበቅባቸውም። ይሁን እንጂ ያልተከተቡ ተጓዦች በራሳቸው ወጪ ሆቴል ውስጥ እስከ 14 ቀናት ድረስ ራሳቸውን ለይተው መቆየት አለባቸው።
በዚህም ሰኞ ብቻ ከ50 በላይ ዓለም አቀፍ በረራዎች ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ተጓዦች ከምዕራብ አውስትራሊያ በስተቀር ወደ ሁሉም ግዛቶች መግባት ይችላሉ።
ምዕራብ አውስትራሊያ እስከ መጋቢት 3 ድረስ ተዘግቶ የሚቆይ ሲሆን ለመግባት ሦስት ክትባቶችን መውሰድ ያስፈልጋል።
የንግድ፣ ቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት ሚኒስትሩ ዳን ቴሃን "ለቱሪዝም ኢንደስትሪያችን እና 660 ሺህ ለሚሆኑ የዘርፉ ሰዎች ድንቅ ዜና ነው" ብለዋል።
አውስትራሊያ እአአ በ2019 ብቻ ወደ 9.5 ሚሊዮን የሚጠጉ የባህር ማዶ ጎብኝዎችን አስተናግዳለች። የእገዳው መነሳት በአገር ውስጥ የጉዞ እገዳዎች ጭምር የተሽመደመደውን የቱሪዝም ዘርፍ እንደሚያነቃቃው ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል ሚኒስትሩ።
የአገሪቱ ጥብቅ እርምጃዎች ቤተሰቦችን በመለየት እና ንግዶች ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ በማሳደሩ ትችት ገጥሞታል። ሆኖም ክትባቶች ከመገኘታቸው በፊት ብዙ ሞትን በመከላከሉ ተወድሷል።
በአውስትራሊያ 4,900 የሚጠጉ ሰዎች በኮቪድ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።












