በኢትዮጵያ በ10 ቀናት 20 ሚሊዮን ዜጎችን ለመከተብ 90 ሺህ የሰው ኃይል ተሰማራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኢትዮጵያ በ10 ቀናት ውስጥ 20 ሚሊዮን ክትባቶችን ለዜጎች ለመስጠት 90 ሺህ የሰው ኃይል እንደተሰማራ ተገለጸ።
የኮቪድ ብሔራዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ፀሐፊ ዶ/ር መሠረት ዘላለም ናቸው ይህን ለቢቢሲ የተናገሩት።
ኢትዮጵያ ውስጥ ክትባት መሰጠት ከተጀመረ ከ11 ወራት በላይ ተቆጥረዋል የሚሉት ዶ/ር መሠረት፤ እስካሁን ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኮቪድ-19 ክትባት እንዳገኙ ነገር ግን በሚጠበቀው መጠን ሰዎች እየተከተቡ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
የክትባት ዘመቻው ከየካቲት 07/2014 እስከ የካቲት 16/2014 ድረስ ዓ.ም. የሚቆይ እንደሆነ ዶ/ር መሠረት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህንን ለማስተባበር ክትባቱ በሚሰራጭባቸው ቦታዎች ከ90 ሺህ በላይ ሙያተኞች እንደተሰማሩም አክለው ገልጠዋል።
የጤና ሚኒስቴር ባለፈው ታኅሣሥ ወር እንዲሁ ተመሳሳይ የክትባት ዘመቻ ጀምሮ ከ5.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን መከተቡ አይዘነጋም።
ዘመቻው የሚያዳርሰው ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ ዜጎችን ሲሆን የመጀመሪያና ሁለተኛ ክትባት እንዲሁም ማጠናከሪያ [ቡስተር] ክትባት እንደሚሰጥም ዶ/ር መሠረት ይናገራሉ።
ለዘመቻው ሦስት ዓይነት ክትባቶች እንደተዘጋጁ የጠቆሙት ፀሐፊዋ እኒህም ጆንሰን ኤንደ ጆንሰን፣ ፋይዘርና ሲኖፋርም እንደሆኑ አመልክተዋል።
ዶ/ር መሠረት ክትባትን አስመለክቶ እየተሠራጩ ያሉ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመከከት "ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው" ይላሉ።
"ከፖለቲካ አመራሮች እንዲሁም ከሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች ጋር በመወያየት እነሱም ክትባት እንዲወስዱ፤ አልፎም ትክክለኛውን መረጃ ለተከታዮቻቸው እንዲያስተላልፉ እንዲያደርጉ እየሠራን ነው።"
አክለው ታዋቂ ሰዎችና መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ሰፊ የማንቃት ሥራ እየተከወነ እንደሆነ ተናግረዋል።
"ማኅበረሰቡን ማስገደድ አንችልም። ምርጫው የራሱ ነው። ነገር ግን ትክክለኛ መረጃ እንዲኖረው እንፈልጋለን።"
ኢትዮጵያ መጀመሪያ ክትባት መስጠት ስትጀምር በስፋት ብዙዎች የወሰዱት አስትራዜኔካ የተሰኘውን ክትባት አንደሆን ይታወቃል።
በዚህኛው ዙር በስፋት ለኅብረተሰቡ እንዲደርስ የተሰራጨው የክትባት ዓይነት አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጠው ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የተባለው ክትባት ነው።
ከዚህ በፊት አስትራዜኔካ አሊያም ፋይዘር እንደ አንደኛ ዙር ክትባት የወሰዱ ሰዎች አሁን ፋይዘርን ለሁለተኛ ጊዜ መወጋት እንደሚችሉ ዶ/ር መሠረት ተናግረዋል።
ማጠናከሪያ የሚሰጣቸው ደግሞ ሲኖፋርም፣ አስትራዜኔካ አሊያም ፋይዘርን ሁለት ጊዜ ወስደው ስድስት ወራት ያለፋቸው ናቸው።
ክትባቱ ኢትዮጵያዊያን ላልሆኑ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩ ለየትኛውም አገር ዜጎች እንደሚሰጥ ከዶ/ር መሠረት ሰምተናል።
ስለክትባቱ የጎንዮሽ ጉዳት የተጠየቁት ሙያተኛዋ ይህንን ጉዳት ለመቀነስ ክትባት የሚያድሉ ሙያተኞች በቂ ሥልጠና እንደተሰጣቸው ያስረዳሉ።
ምናልባት ክትባቱ የሚያስከትለው የጎንዮሽ ጉዳት ካለ ደግሞ ሪፖርት እንዲደረግ ክትባቱን ለሚሰጡ የዘርፉ ሰዎች እንደተነገራቸው ገልጸዋል።
ቢሆንም ክትባቱ አገር ቤት ከመግባቱ በፊት አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎለት እንዳለፈ ጠቁመዋል።
በክልል ደረጃ የትኛው ክልል ዝቅ ያለ ክትባት ደረሰው ተብለው የተጠየቁት የብሔራዊው ማስተባበሪያ ዋና ፀሐፊ ዶ/ር መሠረት የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ተደራሽ እንዳልሆኑ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
"በተለይ ታኅሣሥ ወር የነበረው ዘመቻ ጦርነት በነበረባቸው ክልሎች እንዳልተከናወነ ይታወቃል። ነገር ግን አሁን የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም እነዚህን አካባቢዎች ለማዳረስ ክትባት አሰራጭተናል። በየብስ ትራንስፖርት ብቻ ሳይሆን በአውሮፕላንም ክትባቱ እንዲሰራጭ አድርገናል።"
ዶ/ር መሠረት በፀጥታ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያዎች ላሉ ዜጎችን ለመድረስ የተለየ ዕቅድ ነድፈን እየተንቀሳቀስን ነው ይላሉ።
"በተለይ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የተባለው ክትባት አንድ ጊዜ ስለሆነ የሚሰጠው በመጠለያ ጣቢያ ላሉ ዜጎቻችን እሱን እንሰጣለን። ምክንያቱም ነገ ወደ ቀያቸው ስለሚመለሱና ይህንን መከታተል አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል ይህንን እየተጠቀምን ነው።"
"መንግሥት በማይሄድባቸው ቦታዎች ላይ ደግሞ ሌሎች የተባበሩት መንግሥታት የተራድዖ ድርጅቶች ድጋፍ ሲያደርጉ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በሚሰጡት አግባብ ሰዉን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው።"
ወረርሽኙ ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ467 ሺህ በላይ ሰዎች በኮቪድ የተያዙ ሲሆን 7426 ሰዎች ደግሞ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የጤና ቀውስ ሕይወታቸው አልፏል።












