የአሜሪካን የኒዩክሌር ምስጢሮች አሳልፈው ሊሰጡ ሞክረዋል የተባሉ ጥንዶች ጥፋተኝነታቸውን አመኑ

ጥንዶቹ፡ ዲያና እና ጆናታን

የፎቶው ባለመብት, CBS

ታትሟል

በአሜሪካ የኒዩክሌር ምስጢሮችን አሳልፈው ሊሰጡ ሞክረዋል የተባሉ ጥንዶች ጥፋተኛ መሆናቸውን አመኑ። ጥንዶቹ ዲያና እና ጆናታን ይባላሉ። ነዋሪነታቸው በአሜሪካ ሜሪላንድ ነው።

የአሜሪካ የባሕር ኃይል መሃንዲስ ሚስት የሆነችው ዲያና ባለቤቷ ጆናታን በኒዩክሌር ኃይል የሚንቀሳቀሱ የባሕር ሰርጓጅ መርከቦችን ምስጢሮች ለውጭ አገር ለመሸጥ በመርዳቷ ጥፋተኛ መሆኗን አምናለች።

የ46 ዓመቷ ዲያና ቶቤ ባሏ በለውዝ ቅቤ በተሰራ ሳንድዊች ውስጥ የመረጃ ካርዱን ከደበቀ በኋላ ምስጥራዊ ቦታ በሚገኝና መረጃዎችን እና ቁሶችን ለመለዋወጥ በሚያገልግል ሳጥን ውስጥ አስቀምጦ ሲሄድ አካባቢውን የሚመለከት መስላ ስትተውን ነበር።

የቀድሞዋ መምህርት ዲያና በዚህ ድርጊቷ እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ እስራት ይጠብቃታል።

የ42 ዓመቱ ባለቤቷ ጆናታን ቶቤም በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል። እርሱም ከ12 አስከ 17 ዓመታት የሚደርስ እስራት ይጠብቀዋል።

ምንም እንኳን ጥንዶቹ የፈፀሙት ወንጀል እስከ እድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጣ ቢሆንም፣ አነስተኛ ቅጣት የተላለፈባቸው ከዐቃቤያነ ሕጎች ጋር ባደረጉት የይግባኝ ስምምነት መሠረት ነው።

የይግባኝ ስምምነት ተከሳሾች ጥፋተኝነታቸውን ሲያምኑ ከዐቃቤ ሕግ ጋር የሚደረግ ድርድር ነው።

ጥንዶቹም በአገሪቷ በጥብቅ የተከለከሉ መረጃዎችን ለማስተላለፍ በማሴር በምዕራብ ቨርጂኒያ በሚገኘው በማርቲንስበርግ የፌዴራል ፍርድ ቤት ጥፋተኛ መሆናቸውን አምነዋል።

እንደ አገሪቷ ፍትሕ መሥሪያ ቤት ከሆነ ጆናታን የውጭ አገር ባለሥልጣን ነው ብሎ ላመነው ግለሰብ መልዕክት በመላክ መረጃ አሳልፎ ለመስጠት ሞክሯል።

ይሁን እንጂ ባለሥልጣን ነው ሲል ያመነው ግለሰብ ራሱን የደበቀ የአሜሪካ ፌደራል ፖሊስ ወኪል ነበር።

ዐቃቤያነ ሕጎቹ ጥንዶቹ ከአገር ለመውጣት መልዕክት እየተላላኩ እንደነበር በመጥቀስም ከአገር ሊወጡ ይችላሉ የሚል ስጋት ውስጥ ነበሩ።

የዲያና ጠበቆች ግን መልዕክቶቹ ለወቅቱ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ያላትን ጥላቻ የገለጸችበት እንደሆነና ምስጢራዊ መረጃዎቹን ለውጭ አገር አሳልፎ ለመሸጥ ከተዘጋጀው ሴራ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

እንደ መርማሪዎቹ ከሆነ ጆናታን ከኒዩክሌር ሰርጓጅ መርከቦች፣ ሰነዶችን ከሥራ ውጪ በማዘዋወር በአንድ ጊዜ ጥቂት ገጾችን ሰብስቦ የደኅንነት ኬላዎችን ማለፍ ይችል ነበር።

ጆናታን " የያዝኳቸውን መረጃዎች ቀስ ብዬ እና በተለመደው የሥራ ሁኔታዬ ውስጥ ሆኘ ለመሰብሰብ በጣም እጠነቀቅ ነበር፤ ስለዚህ ማንም እቅዴን አይጠራጠርም" ሲል ለውጭ መንግሥት ይሰራል ብሎ ላመነው ግለሰብ [በስውር ለሚከታተለው ግለሰብ] ጽፎ ነበር።

በወቅቱ ጆናታን በግለሰቡ ላይ እምነት ስለነበረው ወጥመድ ውስጥ መግባቱን አላወቀም ነበር።

ጆናታን በሌላኛው መልዕክቱም ከግለሰቡ ጋር ስላላቸው ወዳጅነት እና ስለወደፊቱ ተስፋው ጽፏል።

"አንድ ቀን፣ ሰላም በሚሆንበት ጊዜ፣ ምናልባት ሁለት የድሮ ጓደኛሞች በካፌ ውስጥ ለመገናኘት፣ በጋራ ወይን ለመጎንጨት እና በጋራ ታሪካቸው ለመሳቅ እድል ይኖረቸዋል" ሲል ነበር የጻፈው።

በእንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ዐቃቤ ሕግ ከተከሳሾች ጋር የይግባኝ ስምምነት ማድረግ የተለመደ አይደለም። ይሁን እንጂ የፌደራል መርማሪዎች ጉዳዩን በጥብቅ እንደያዙት የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

መርማሪዎቹ ከጥንዶቹ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት አነስተኛ ቅጣት እንዲጣልባቸው ሊፈልጉም ይችላሉ።

በዚህ ጉዳይ ላይ በኒውዮርክ የኮሎምቢያ የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ዳንኤል ሪችማን "አንዳንድ ጊዜ ዐቃብያነ ሕጎች ተከሳሾች በስለላ ሥራቸው ላይ ሊረዳቸው የሚችል ነገር እንዲናገሩ ለማድረግ ከፍተኛውን ቅጣት ያስቀሩታል" ብለዋል።

በጥንዶቹ ጉዳይም ላይ መርማሪዎች ከተከሳሾች አንድ ነገር ለማወቅ ፈልገዋል።

የአሜሪካ የባህር ኃይል

የፎቶው ባለመብት, US NAVY/THIEP VAN NGUYEN II

እንደ ፌደራል መርማሪዎች ከሆነ ጆናታን በኑክሌር ሚስጢሮቹ ምትክ በክሪፕቶከረንሲ የሚከፈል 100 ሺህ ዶላር ጠይቆ ነበር።

በይግባኝ ስምምነታቸው መሠረትም ጥንዶቹ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ያደረጋቸውንና በፌደራል ምርመራ ወቅት ተልኮላቸው የነበረውን ክሪፕቶከረንሲ ለመመለስ ፌደራል ፖሊስን እንደሚረዱ ተናግረዋል።

ጥንዶቹ፡ ዲያና እና ጆናታን

ጆናታን በአገሪቱ ውስጥ በጥብቅ ቁጥጥር ከሚደረግባቸው ምስጢሮች አንዱ በሆነው ለባሕር ሰርጓጅ መርከቦች የኃይል ምንጭ በሚሆነው የኒውክሌር ሥርዓት ውስጥ ባለሙያ ነበር።

ጥንዶቹ ጥቅምት ወር ላይ በቁጥጥር ሥር ከመዋላቸው በፊት ከሁለቱ ልጆቻቸው ጋር የአሜሪካ የባሕር ኃይል አካዳሚ መገኛ በሆነችው ሜሪላንድ በአናፖሊስ ይኖሩ ነበር።

ዲያና በአንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ የታሪክና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ታስተምር ነበር። በአትላንታ ከሚገኘው ኢሞሪ ዩኒቨርሲቲም በአንትሮፖሎጂ የሦስተኛ ዲግሪ ምሩቅ ናት።

ጆናታን ቶቤ የጦር ተጠባባቂ አባል ከመሆኑ በፊት በባሕር ኃይሉ ውስጥ አገልግሏል።

በቨርጂኒያ በሚገኘው አርሊንግተን የባሕር ኃይል ኦፕሬሽን ዋና ኃላፊ ቢሮ ውስጥም ሰርቷል።