ለሶስት ዓመታት ጠፍታ የነበረች አሜሪካዊት ህፃን በሚስጥራዊ ክፍል ውስጥ በህይወት ተገኘች

ፔዝሊ ሹልቲስ

የፎቶው ባለመብት, Saugerties Police

ታትሟል

ለሶስት ዓመታት ያህል ጠፍታ የነበረች አሜሪካዊት ህፃን በአንድ ቤት ውስጥ በደረጃ ስር በሚገኝ ሚስጥራዊ ክፍል ውስጥ እንደተገኘች የኒውዮርክ ግዛት ፖሊስ አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት ስድስት ዓመት የሆናት ፔዝሊ ሹልቲስ ሰኞ እለት ሳውገርቲስ በተሰኘች ከተማ ውስጥ በአንድ ቤት ውስጥ በተደረገ ፍለጋ ተገኝታለች ተብሏል።

ህፃኗ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደምትገኝ የተገለጸ ሲሆን ከህጋዊ አሳዳጊዎቿ እና ከታላቅ እህቷም ጋር መገናኘቷን ፖሊስ ተናግሯል።

አሳዳጊ ያልሆኑት ወላጆቿ በህፃኗ እድገት ላይ ጣልቃ በመግባት እና የልጅን ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል ክስ ተከሰዋል።

ፔዝሊ ሹልቲስ በኒውዮርክ ከምትገኘው ቲዮጋ ግዛት የጠፋችው በአውሮፓውያኑ 2019 እንደነበር የፖሊስ መግለጫ አስታውቋል። በወቅቱ ህፃኗ አራት ዓመቷ ነበር።

በወቅቱም ባለስልጣናቱ በወላጆቿ የ33 ዓመቷ ኪምበርሊ ኩፐር እና የ32 ዓመቱ ሹልቲስ ጁኒየር እንደተወሰደችም ያምኑ ነበር።

ህፃኗ በሳውገርቲስ ከተማ በተደበቀ ቦታ እንደምትገኝ ፖሊስ መረጃ ማግኘቱን ተከትሎ ፖሊሶች ቤታቸውን ፈትሸዋል። የግለሰቦቹ ቤት ከዚህ ቀደም ተፈትሾ ነበር።

የቤቱ ባለቤት የሆነው የ57 አመቱ ኪርክ ሹልቲስ ፖሊስ ቤቱን በሚፈትሽበት ወቅት በቦታቸው የነበረ ሲሆን ህፃኗ የት እንዳለች ምንም እንዳማያውቅም ለፖሊስ ተናግሯል።

ነገር ግን ፖሊስ ፍተሻ ከጀመረ ከአንድ ሰዓት በኋላ ከመርማሪዎቹ አንዱ ወደ ምድር ቤት የሚወስደው ደረጃ እንግዳ በሆነ መልኩ እንደተሰራ አስተዋለ።

ፖሊሶች የቆሙ ጣውላዎችን ካስወገዱ በኋላም ህፃኗን እና ወላጅ እናቷን ኪምበርሊ ኩፐርን ተደብቀው አግኝተዋቸዋል።

ፖሊሶች ስፍራውን "ትንሽ፣ ቀዝቃዛ እና እርጥብ" ነው ሲሉ ነበር የገለጹት።

ፔዝሊ በህክምና ባለሙያዎች የተመረመረች ሲሆን በጥሩ ጤንነት ላይ እንደምትገኝ ተዘግቧል።

ወላጆቿ እንዲሁም አያቷ ህፃኗን በመሰወር ተይዘው በቁጥጥር ስር ውለው ነበር።

አያትየው እና ወላጅ አባቷ የፍርድ ሂደቱንም ከውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ተለቀዋል።

ወላጅ እናቷ ኪምበርሊ ኩፐር ከዚህ ቀደምም የእስር ማዘዣ ወጥቶባት ስለነበር ክሷን በእስር ላይ ሆና እንድትከታተል ተወስኗል።

ምርመራው እንደቀጠለ ፖሊስ ተናግሯል።