በሶማሊያ ምርጫ ዋዜማ አንድ አጥፍቶ ጠፊ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ቀጠፈ

ጠመንጃ የያዘ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ሶማሊያ ውስጥ አንድ አጥፍቶ ጠፊ ባፈነዳው ቦምብ ቢያንስ 10 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

አጥፍቶ ጠፊው ጥቃቱን ያደረሰው ሶማሊያ ምርጫ ለማካሄድ አንድ ቀን ሲቀራት ነው።

ፍንዳታው የደረሰው በልደወይኔ በተሰኘችው ማዕከላዊ ሶማሊያ በምትገኝ ከተማ ሲሆን የከተማዋ ባለሥልጣና በሚያዘወትሩት አንድ ሬስቶራንት ውስጥ ነው ጥቃቱ የተፈፀመው።

ሮይተርስ የተሰኘው የዜና ወኪል እንደዘገበው ከሟቾቹ መካከል ለሶማሊያ ፓርላማ ለመመረጥ ዕጩ የነበሩ ግለሰብ ይገኙበታል።

የአል-ሸባብ ታጣቂዎች ጥቃቱን የፈፀምነው እኛ ነን ብለዋል።

ፅንፈኛው ቡድን አል-ሸባብ የሶማሊያ መንግሥትን ከአስር ዓመት በላይ ሲዋጋ ቆይቷል። በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎችም ጠንካራ ይዞታ መሥርቷል።

ቡድኑ በተለይ በቅርብ ጊዜያት በርካታ ጥቃቶችን እየሰነዘረ ይገኛል።

ኤኤፍፒ የተባለው የዜና ወኪል፤ የፓርላማ ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጀች ባለችው በልደወይኔ ከተማ የፀጥታ ኃይሎች በርከት ብለው ተሰማርተዋል ሲል ፅፏል።

የሶማሊያ ምርጫ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በፕሬዝደንቱ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ለወራት ሲጓተት ቆይቷል።

የፓርላማ ምርጫው በሚቀጥለው ሳምንት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በሶማሊያ ምርጫ መሠረት የጎሳ መሪዎችና ሌሎች ተወካዮች ሕግ አውጭዎችን ከመረጡ በኋላ እኒህ ተመራጮች ደግሞ በተራቸው ፕሬዝደንት ይመርጣሉ።