በባህሬን ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የተደረገው ደማቅ አቀባበል

የባህሬን ንጉስ ሃማድ አል ካሊፍ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የባህሬን ንጉስ ሃማድ አል ካሊፍ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት።
ታትሟል

የባህሬን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሙዚቃ ቡድን ከዚህ ቀደም የእስራኤል ብሔራዊ መዝሙርን ስለመጫወቱ እርግጥ አይደለም። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ባህሬን በደረሱ ወቅት ግን ማርሽ ቡድኑ ያሰማው ዜማ 'ፍጹም' የሚባል ነበር ተብሎለታል።

የእስራኤል ብሔራዊ መዝሙር በቤተ-መንግሥት ዘብ አጀብ ደምቆ በባህሬን አልጋወራሽ ሰልማን ቢን ሃማድ እና በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ፊት ተሰምቷል።

ይህ ከጥቂት ዓመታት በፊት ይሆናል ተብሎ አይጠበቀም ነበር። እስራኤል ከአረብ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት እያደሰች፤ እውን የማይመስሉ እውነታዎችን ለዓለም እያስመለከተች ነው።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በጥቂት ወራት ውስጥ ወደ ባህረ ሰላጤ አገር ሲሄዱ ይሄ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ናፍታሊ ቤኔት ወደ ባህሬን ለመጀመሪያ ጊዜ ከመሄዳቸው ከሁለት ወራት በፊት ወደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች አቅንተው ነበር። ሁለቱም አረብ አገራት ከእስራኤል ጋር በመከላከያ እና ንግድ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ፊርማቸውን አኑረዋል።

እስራኤል ከአረብ አጋረት ጋር ያላትን ወዳጅነት ለማሻሻል ጥረት ማደረግ የጀመረችው በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልት ትራምፕ አሸማጋይነት ነበር።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ባህሬን ከደረሱ በኋላ ከአገሪቱ የፋይናንስ፣ የውጪ ጉዳይ እና ትራንስፖርት ሚኒስትሮች ጋር ተገናኘተው መክረዋል። ቤኔት ከባህሬን ንጉስ እና ልዑል አልጋ ወራሸ ጋርም ተገናኝተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኔት ጉብኝት ዓላማ በሁለቱ አገራት መካከል "ሰላም፣ መረጋጋት እና ብልጽግናን" ማምጣት ያለመ ስለመሆኑ በሁለቱ አገራት ባለስልጣናት ተነግሯል።

እስራኤል ከባህሬን በተጨማሪ ከተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እና ሞሮኮ ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው በንግድ እና ቱሪዝም ዘረፍ ላይ አብሮ ለመስራት ከስምምነት ደርሳለች።

የጦር ትብብርን በተመለከተ ግን እስራኤል ከአረብ አገራት ጋር ስለደረሰችው ስምምነት ዝርዝር ጉዳይ አልተገለጸም።

ልዑል አልጋ ወራሽ ሰልማን ቢን ሃማድ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ልዑል አልጋ ወራሽ ሰልማን ቢን ሃማድ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት።

በነዳጅ ሃብቷ የበለጸገችው ባህሬን እንደ ተቀሩት ጎረቤት የባህረ ሰላጤ አገራት የገቢ ምንጯን ከነዳጅ ወደ ተለየ ዘርፍ ለመቀየር ጥረት እያደረገች ነው። የባህሬን መዲና ማናማ በረዣዥም ሕንጻዎች፣ የገበያ አዳራሾች እና ቅንጡ ሆቴሎች ያሸበረቀች ናት።

እስራኤል እና የባህረ ሰላጤው አገራት ጸረ ኢራን የሆነ ጠምር ኃይል ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ይመስላል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኔት ኢራን 'የጋራ ስጋታችን' ነች ይላሉ። ለዚህም በእስራኤል እና በአረብ አገራት መካከል 'ወዳጅነት' መመስረት አለበት ይላሉ።

ይሁን እንጂ በተለይ በባህሬን ከእስራኤል ጋር የተጀመረውን ወዳጅነት የሚቃወሙት በርካቶች ናቸው። የባህሬን ሱኒ ሙስሊም ንጉሳዊ አስተዳደር ብዙሃኑን ሺዓ ሙስሊሞች ያስተዳድራል። አብዛኛው የሺዓ ሙስሊም ከእስራኤል ጋር የተጀመረውን ወዳጅነት አይደግፍም። ቁጥራቸው አናሳ ቢሆንም በመዲናዋ ማናማ ሰኞ ምሽት ላይ ጸረ መንግሥት ተቃውሞዎች ተሰምተዋል።

ባህሬን ዋነኛ የመንግሥት ተቀናቃኝ ቡድን ሕገ-ወጥ ነው ስትል ፈርጀዋለች። ምንም እንኳ ባህሬን የሰዎችን መብት አከብራለሁ ብትልም አንድ ጥናት አገሪቱ የማሕብረሰብ አንቂ ሰዎችን ተንቀሳቃሽ ስልክ በእስራኤል ሰራሹ 'ፔገሰስ' ሶፍትዌር ጠልፋለች።

ከአገሪቱ ዜጎች በተጨማሪ ፍልስጤማውያን የእስራኤል ከአረብ አገራት ጋር ወዳጅነት መጠናከር አላስደሰታቸውም። መድራችን በእስራኤል ተቀምተናል የሚሉት ፍልስጤማውያን ከእስራኤል ጋር ግነኙነታቸውን እያደሱ ባሉ አረብ አገራት ተከድተናል ይላሉ።