ሩሲያ ጦሬን ከድንበር አንቀሳቅሻለሁ ብትልም ባይደን የወረራ ስጋት እንዳለ ነው አሉ

ፕሬዝደንት ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ሩሲያ ዩክሬን ድንበር አቅራቢያ አሰማርታ ከነበረው ጦር መካከል የተወሰነው ወደ ኋላ መልሻለሁ ብትልም ፕሬዝደንት ባይደን ግን ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር ትችላለች የሚለው ስጋት እንዳለ ነው አሉ።

ፕሬዝደንት ባይደን የሩሲያ ወረራ የማጋጠም እድሉ እንዳለ ነው ካሉ በኋላ ወረራውን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለው ሰብዓዊ ቀውስ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችልም አሳስበዋል።

አሜሪካንን ጨምሮ ምዕራባውያን ሩሲያ በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ 150ሺህ ወታደሮች አሰማርታለች ይላሉ።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር በበኩላቸው አገሪቱ ወደ ድንበር ካስጠጋቻቸው የጦር አባላት የተወሰኑትን ማንቀሳቀሳቸውን ገልጸዋል። ባይደን ግን ይህ አልተረጋገጠም ብለዋል።

ባይደን "[የሩሲያ ወታደሮች] አካባቢውን ለቅቀው መውጣታቸው መልካም ነገር ቢሆንም ይህ ስለመሆኑ ግን አልተረጋገጠም" ሲሉ ተናግረዋል።

"የእኛ ተንታኞች ስፍራው አሁንም አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ያመለክታሉ" ብለዋል ፕሬዝደንት ባይደን።

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በተመሳሳይ ከሩሲያ አቻቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር በነበራቸው የስልክ ንግግር፤ ሩሲያ ጦሯን ከዩክሬን ድንበር ስለማንቀሳቀሷ ማረጋገጫ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል።

ይህ የባይደን ንግግር የተሰማው ቭላድሚር ፑቲን አስተዳደራቸው ለአገሪቱን የደህንነት ጉዳይ አጽንኦት ሰጥቶ እንደሚመለከት ከተናገሩ በኋላ ነው።

ቭላድሚር ፑቲን አገራቸው ሩሲያ ዩክሬንን የመውረር ፍጹም ፍላጎት እንደሌላት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተሰምተዋል። ይሁን እንጂ ፑቲን ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮቻቸውን ወደ ዩክሬን ማስጠጋታቸው በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ፈጥሯል።

ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) እንደማትቀላቀል ፑቲን ማረጋገጫ ይፈልጋሉ። ፑቲን በቀጠናው የኔቶ መጠናከርን ለሩሲያ እንደስጋት ይመለከቱታል። ኔቶ ግን ይህን የሩሲያ ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።

"የአሜሪካ ሕዝብ ዴሞክራሲን እና ነጻነት ለማረጋገጥ የሚከፈለውን ዋጋ ይረዳል። ይህ ያለ ሕመም እንደማይመጣ ለማስመሰል አልጥርም" ሲሉ ፕሬዝደንት ባይደን ተናግረዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ደግሞ የአገራቸው የደህንነት ምንጮች ሩሲያ በድንበር አቅራቢያ ጊዜያዊ ሆስፒታሎችን እየገነባቸው እንደሆነ አመላክተዋል ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ የሩሲያ የሆስፒታል ግንባታ የወረራ እቅድ መኖሩን የሚያሳይ ነው ብለዋል።