ኮሮናቫይረስ፡ የኢትዮጵያ የአበባ ምርት ፍላጎት በአውሮፓ እያንሰራራ ነው ተባለ

ታትሟል

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ በመታት በአውሮፓ ውስጥ የበሽታው ጉዳት እየቀነሰ መምጣቱ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ የአበባ ምርት ተፈላጊነት እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ።

ከቻይና በመቀጠል የኮሮናቫይረስ በበርካታ የአውሮፓ አገራት ውስጥ ተዛምቶ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በወረርሽኙ በመያዛቸው በንግድና በእንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት ፈጥሮ ነበር።

በሽታው በርካታ ሰዎችን የገደለባቸው አገራት በወረርሽኙ መስፋፋት ላይ ለውጥ በመታየቱ የእንቅስቃሴ ገደቦች ላልተው ወደ መደበኛ ህይወት ለመመለስ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ለኢትዮጵያ አበቦች ያለው ፍላጎት እየተሻለ መምጣቱ ተነግሯል።

አውሮፓ ውስጥ በበሽታው ምክንያት ተቀዛቅዞ በነበረው የአበባ ፍላጎት ላይ ጥሩ ለውጥ እንዳለ የተናገሩት የኢትዮጵያ አበባ አትክልት እና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴወድሮስ ዘውዴ ናቸው።

ዋና ዳይሬክተሩ ከእንቅስቃሴ ገደቦች መላላት ጋር ተያይዞ በአውሮፓ ገበያ ላይ ለኢትዮጵያ አበቦች ያለው ፍላጎት ከማንሰራራቱ ጋር ተያይዞ በገበያም ሆነ በዋጋ በኩል ጭማሪ መኖሩን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከየካቲት ወር ጀምሮ አስደንጋጭ የሚባል የገበያ እና ዋጋ መውደቅ እንደነበር የተናገሩት አቶ ቴወድሮስ በተያዘው የግንቦት ወር ላይ የፍላጎትና የዋጋ መሻሻል አለ ብለዋል።

በተለይ ለኢትዮጵያ አበባ ትልቅ የገበያ መዳረሻ ናቸው የሚባሉት እንደጀርመን እና ስዊትዘርላንድ ያሉት አገራት ድንበሮቻቸውን መክፈታቸውና የእንቅስቃሴ ገደቦች መላላታቸው ለአበባ ገበያው ማንሰራራት ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አገራቱ ከወሰዷቸው እርምጃዎች በተጨማሪ "ከእናቶች ቀን መከበር ጋር ተዳምሮ ገበያው ላይ መነቃቃት ፈጥሯል" ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጨምረውም አሁን ካሉት ተስፋ ሰጪ ለውጦች በተጨማሪ ሌሎችም አገራት ድንበሮቻቸውን ሲከፍቱና የጣሉትን የእንቅስቃሴ ገደቦች ሲያላሉ የአበባ ፍላጎትና ዋጋው መሻሻሉን ይቀጥላል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

በኮሮናቫይረስ ምክንያት የአበባ ልማት ዘርፍ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ መንግሥት በብድር፣ በጉምሩክ እና በሌሎች ተያያዥ ዙሪያ ላቀረቡት ጥያቄ ፈጣን ምላሽና ድጋፍ እንደሰጣቸው ጠቁመዋል።

አቶ ቴዎድሮስ እንዳሉት ባለፉት ወራት አምራቾች ቀላል የማይባል ፈተና ገጥሟቸው እንደነበር አስታውሰው፤ ነገር ግን በዚህ ሳቢያ የአበባ እርሻዎች ሰራተኞችን አለመቀነሳቸውን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በምርቶች ፍላጎት ላይ መሻሻሎች እየታዩ በመሆናቸው የአበባ እርሻዎች ሙሉ ለሙሉ ወደ መደበኛ ሥራቸው እየገቡ መሆናቸውንም አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ ተናግረዋል።