ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"በመጠጥ ምክንያት የራሴን አሊያም የሌላ ሰው ሕይወት ላጠፋ እችል ነበር" ዋይን ሩኒ
የእንግሊዝና ማንቸስተር ዩናይትድ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪው ዋይን ሩኒ አንድ ሰሞን በተጠናወተው የመጠጥ ሱስ ሳቢያ ሊሞት አሊያም የሰው ሕይወት ሊያጠፋ ይችል እንደነበር ይፋ አድርጓል።
አሁን ደርቢ ካውንቲ የተሰኘው ቡድን አሠልጣኝ የሆነው ሩኒ ከ'ቢቢሲ ብሬክፋስት' ፕሮግራም ጋር በነበረው ቆይታ ነው ይህን ያለው።
የዋይን ሩኒ ሕይወት የሚቃኝ አዲስ ዘጋቢ ፊልም በቅርቡ ይለቀቃል።
ሩኒ በመጠጥና በአእምሮ ጤና ሳቢያ ያሳለፋቸውን የጨለማ ጊዜያት በማስታወስ እጅግ ያስፈራው የነበረው ነገር "ሞት" እንደነበር ተናግሯል።
ስለፈፀማቸው "ስህተቶች" ሲናገር "ሴቶች ሊሆኑ ይችላሉ፤ አሊያም ጠጥቶ ማሽከርከር፤ የሰው ነብስ ላጠፋ ሁላ ነበር፤ የራሴን ነብስ ላጠፋም እችል ነበር። በዚህ ዓይነት የሕይወት ውጣ ውረድ ማለፍ ይከብዳል" ብሏል።
"እርዳታ ያስፈልገኝ እንደነበር አውቃለሁ። ራሴን አልፎም ቤተሰቦቼን ለመታደግ።"
ሩኒ አክሎ እንደ እግር ኳስ ተጫዋችነቱ ብዙ ነገሮችን ከማውራት ይልቅ መደበቁ እንደሚያዋጣው ያስብ እንደነበር ገልጧል።
"ከዛሬ 10 አሊያም 15 ዓመት በፊት ወደ መልበሻ ክፍል ሄጄ 'የመጠጥ ችግር አለብኝ፤ የአእምሮ ጤናዬ ትክክል አይደለም' ማለት አይታሰብም ነበር። ላደርገው አልችልም።"
'ሩኒ' የተሰኘው ዘጋቢ ፊልም አማዞን ፕራይም ቪድዮ በተሰኘው አውታር ላይ ተለቋል። ፊልሙ የሩኒን ታሪክ ከልጅነቱ አሁን እስካለበት የአሠልጣኝነት ዘመን ድረስ ይተርካል።
ለመሆኑ ከዚህ ዘጋቢ ፊልም ጎልተው የወጡና መነጋገሪያ የሆኑት የሩኒ ድርጊቶች የትኞቹ ናቸው?
ድብድብና መጠጥ
ሩኒ በዚህ ዘጋቢ ፊልም ላይ ታዳጊ እያለ 'መልካም' የሚባል እንዳልነበር ይናገራል። ብዙ ጊዜ አመፅ የማያጣው እንደነበርም ይተርካል።
"በ12 ዓመቴ ተደባድቤ ዓይኔን ታሽጌ የመጣሁበት ጊዜ ነበር።"
አልፎም ዝነኛው እግር ኳስ ተጫዋች ታዳጊ ሳለ ወደ ሙዚቃ ድግሶች ሄዶ አመፅ ያስነሳ እንደነበርም ይናገራል።
በአንድ ወቅት በኤቨርተን የታዳጊዎች ካምፕ ውስጥ ኮሊን ሃርቪ የተባሉት አሠልጣኝ ይዘውት በጣም ተሰጥዖ ያለው ተጫዋች እንደሆነ በመንገር ይህንን ብቃቱን እንዳያባክነው እንደመከሩት ያስታውሳል።
ዋይን፤ በፕሪሚዬር ሊጉ ወጣቱ ጎል አስቆጣሪ ለመሆን ቆርጦ ተነስቶ እንደነበርም ያስታውሳል።
ሩኒ ለኤቨርተን ያስቆጠራት የመጀመሪያ ጎል
በፈረንጆቹ ጥቅምት 2002 ሩኒ ራሱን ለዓለም አስተዋወቀ።
ዋይኒ ሩኒ 17ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ሊያከብር 5 ቀናት ሲቀሩት፣ ኤቨርተን ከአርሰናል የሚያደርጉት ግጥሚያ፣ አርሰናል በወቅቱ ለ30 ጨዋታዎች ሳይሸነፍ እየገሰገሰ ነበር። እነ ቲዬሪ ሄንሪ፣ ፓትሪክ ቪዬራ፣ ዴቪድ ሲማን እና ሶል ካምፕቤል የነገሱበት ዘመን።
ሩኒ እኒህ ተጫዋች በወቅቱ ምን ያህል ድንቅ እንደነበሩ ያስታውሳል። ነገር ግን በዚህ ጨዋታ ላይ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ቋምጦ ነበር።
"ይህ በ16 ዓመቴ የማደርገው የመጨረሻው ጨዋታዬ ነው። በ16 ዓመቴ ጎል ማስቆጠር አለብኝ ብዬ አሰብኩ" ይላል ሩኒ።
ተቀይሮ የገባው ሩኒ ጭንቅላቱ ውስጥ የሚያቃጭለው አንድ ነገር ብቻ ነው። "ዕድሉን ካገኘሁ ከየትም ቢሆን ወደ ጎል እመታለሁ" የሚል ድምፅ።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ግድም ሩኒ ኳሱን እየገፋ ሲሄድ ካምፕቤል ማፈግፈግ ጀመረ። ይህን አጋጣሚ የተመለከተው ሩኒ ኳሷን አክርሮ ወደ ጎል ነረታት። ጉዲሰን ፓርክ በአንድ እግሩ ቆመ።
"ይሄን ስም አስታውሱት፤ ዋይን ሩኒ" ይባላል ሲል የጨዋታው አዳማቂ ክላይቭ ቲልደስሊ አወጀ።
የ18 ዓመቱ ኮከብ
ዋይን ሩኒ በ18 ዓመቱ በአውሮፓ መድረክ ጎልቶ መውጣት ጀመረ።
በ2004 ፖርቹጋል ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ድንቅ ብቃቱን ቢያሳይም በሩብ ፍፃሜው ባጋጠመው ጉዳት እሱ ከሜዳ ሲወጣ አገሩ እንግሊዝም ከውድድሩ ተሳነበተች።
በ18 ዓመቱ እነ ዚነዲን ዚዳንና ቲዬሪ ሄንሪ ከያዘው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ጋር እንግሊዝ በነበራት ግጥሚያ ያሳየው ጥበብ እስከዛሬም በእግር ኳስ አድናቂዎች ዘንድ ይዘከራል።
በወቅቱ አሉ ከሚባሉ ተከላካዮች መካከል የነበረው ሊሊያም ቱራም በሩኒ የኳስ ጥበብ በአውሮፓ ሕዝብ ፊት ተዋረደ።
ምንም እንኳ እንግሊዝ ይህን ጨዋታ 2 ለ 1 ብትሸነፍም እንደ ሄንሪ ሳይቀር ለሩኒ ያላቸውን አድናቆት አልደበቁም።
ዋይንና ኮሊን ሩኒ
ዋይንና ኮሊን ሩኒ በግልፅ ስለ ሩኒ አለመታመን በዚህ ዘጋቢ ፊልም ላይ ይተርካሉ።
"እርግጥ ነው በጣም መጥፎ ቦታ ነበርኩ። አልኮል ሲጨመርበት ደግሞ መጥፎ ውሳኔ ትወስናለህ። የዚህን ውሳኔ ውጤት መቀበል ደግሞ ግድ ነው። ነገር ግን ለኮሊን ያለኝን ፍቅር አይወስደውም።"
ኮሊንም የሩኒ የመጠጥ ፍቅር ብዙ ችግር አምጥቶ እንደነበር ታነሳለች።
የሩኒ ሚስት ኮሊን ጥንዶቹ እንዴት አድርገው በመወያየት ችግሮቻቸውን ይፈቱ እንደነበር በዚህ ዘጋቢ ፊልም ላይ ትተርካለች።
ስለዘጋቢው ፊልም ለቢቢሲ የተናገረው ሩኒ ከሚስቱ ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላቸው፤ አልፎም ሚስቱ ጓደኛውም ጭምር እንደሆነች፤ አሁን ደግሞ የአራት ልጆች ወላጅ ሆነው እንዴት እንደሚዘልቁ ያጋራል።
"ኮሊን ጥላኝ ልትሄድ የምትችልባቸው አጋጣሚዎች ነበር። ነገር ግን እንዋደድ ነበር።"
"ሰዎችን አማከርኩ። እሱ አገዘኝ። ውስጥ ያለውን ነገር ማውጣት ተገቢ ነው። ስታምቀው እያደር ይጎዳሃል።"
ከቼልሲ ጋር በነበረው ጨዋታ ሰው 'መጥረብ' አስቤ ነው የገባሁት
በፈረንጆቹ 2006 የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የሆዜ ሞሪንሆ ቼልሲ ማንቸስተር ዩናይትድን ይገዳደር ጀመር።
ሚያዚያ 2006 ቼልሲና ማንቸስተር ዩናይትድ በስታንፈርድ ብሪጅ ጨዋታ ነበራቸው። ቼልሲ ዋንጫውን ለማንሳት የሚፈልገው አንድ ነጥብ ብቻ ቢሆንም ግጥሚያውን 3 ለ 0 አሸነፈ።
ይህ ለሩኒ እጅግ ከባድ ነበር።
"አዲስና ትላልቅ እሾህ [ብሎን] ያለው ጫማ አድርጌ ገባሁ። ብሎኖቹ የሚፈቀዱ ቢሆንም ከዚያ ቀደም ካደረግኳቸው ተለቅ ያሉ ነበሩ።"
በዚህ ጨዋታ ከሩኒ ጋር የተጋጨው ፍራንክ ላምፓርድ እግሩ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ክራች እስከመጠቀም ደርሶ እንደነበር ይታወሳል።
ከሮናልዶ ጋር ምንም ጉዳይ አልነበረኝም
ሩኒ በ2006 የዓለም ዋንጫ እንግሊዝ ከፖርቹጋል ስትጫወት ሮናልዶ ቢጫ እንዲያገኝ ማድረጉን ተናዟል።
ይህ የዓለም ዋንጫ እንግሊዛዊያን የሚረሱት አይደለም። በሩብ ፍፃሜ ከፖርቹጋል የተገናኘችው እንግሊዝ ተሸንፋ መውደቋ አይረሳም።
በዚህ ጨዋታ ሩኒ ሪካርዶ ካርቫልሆ ላይ በፈፀመው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቶ ነበር።
ሩኒ ጥፋቱን በፈፀመበት ወቅት የክለብ አጋሩ ሮናልዶ ዳኛው ለሩኒ ቀይ ካርድ እንዲሰጡ ሲወተውት ይታያል።
ዋይን ሩኒ በዚህ ጨዋታ ተሰናብቶ ከወጣ በኋላ መልበሻ ክፍል ውስጥ ራሱን እንደወቀሰ ይናገራል።
ነገር ግን ከዚህ ክስተት በኋላ ሩኒ ለሮናልዶ ምንም ቂም እንዳልያዘበትና ትኩረታቸውን ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ አድርገው ዋንጫ ማንሳት እንዳለባቸው እንደነገረው በፊልሙ ያነሳል።
ሁለት ወጣት ከዋክብት በቀጣዩ ዓመት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን ማንሳት ችለዋል።