የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከግድያ ሙከራ አመለጡ

ታትሟል

የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሃሚድ አል-ዴኢባህ ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ ማምለጣቸው ተገለጸ።

ዛሬ ሐሙስ የካቲት 03/2014 ንጋት ላይ በመዲናዋ ትሪፖሊ በመኪናቸው ላይ ተኩስ ተከፍቶ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩን የያዘችው በኪና በተደጋጋሚ በጥይት እየመታች በትሪፖሊ ጎዳናዎች ላይ ስትሸከረከር ነበር ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግደል የሞከሩት ጥቃት አድራሾች ከጥቃቱ በኋላ ከስፍራው የተሰወሩ ሲሆን ማንነታቸውም እስካሁን አልታወቀም ተብሏል።

ይህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የግድያ ሙከራ የተፈጸመው በምሥራቅ አገሪቱ የሚገኘው ምክር ቤት ዛሬ የካቲት 3 ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚተካ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ ቀጠሮ በያዘበት ወቅት ነው።

ፓርላማው ዛሬ በያዘው ቀጠሮ ደስተኛ ያልሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሃሚድ አል-ዴኢባህ፤ የፓርላማው የድምጽ ውጤት ምንም ይሁን ምን እንደማይቀበሉት ቀደም ሲል ተናግረው ነበር።

ከቀድሞ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ግድያ በኋላ ሊቢያ ሰላም እና መረጋጋት እርቋት ቆይታለች። የተለያዩ የታጠቁ ቡድኖች የሊቢያን ማዕከላዊ መንግሥት ለመቆጣጠር እንዲሁም በሊቢያ ፍላጎት ያላቸው የውጭ አገር መንግሥታት ፍላጎትን ለማሳካት እርስ በእስር ሲዋጉ ቆይተዋል።

በተባበሩት መንግሥታት እውቅና የተሰጠው መንግሥት እና በተጽእኖ ፈጣሪው ጄነራል ካሊፍ ኻፍታር የሚመራው አማጺ በሊቢያ ዋነኛ ተቀናቃኝ ኃይሎች ናቸው።

በሊቢያ የሚንቀሳቀሱት ኃይሎች የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የሌሎች የውጭ አገራት ፍላጎትን ለማሳካት ነፍጥ አንስተዋል።

ጄነራል ኻፍታር "እስላማዊ አሸባሪዎችን" እዋጋለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ጆርዳን ጽንፈኞች ከቀጠናው መጽዳት አለባቸው በማለት አጋርነታቸውን ከጄነራሉ ጋር አድርገዋል።

ከእነዚህ አገራት በተጨማሪ፤ ጎረቤት አገር ግብፅም የጄነራሉ አጋር ነች። አል ሲሲ ከዚህ ቀደም ለጄነራል ኻፍታር ጦር የሎጂስቲክ ድጋፎችን አድርገዋል።

ከአካባቢው አገራት በተጨማሪም ሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች ከጄነራሉ ጎን ተሰልፈው እንዲዋጉ ማድረጓ በቅርቡ ተመልክቷል።

በሌላኛው በኩል ደግሞ ቱርክ በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ለተሰጠውን መንግሥት ድጋፍ ታደርጋለች። ቱርክ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጦሯን ወደ ሊቢያ ልካ የኃይል ሚዛኑ ዓለም አቀፍ እውቅና ወደ ተሰጠው መንግሥት እንዲያጋድል አድርጋለች ።