ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቻይናው መሪ ለምን ወደ ሰሜን ኮሪያ ተጓዙ?
ለቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ሰሜሪን ኮሪያ መቆጣጠር የማትችላት ወይም ልታጣት የማትችላት ጎረቤት ናት።
ሁለቱ አገራት በተደጋጋሚ ወዳጅነታቸውን "በደም የተመሰረተ" ሲሉ የኮሪያን ጦርነት በመጥቀስ ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ በቅርብ ዓመታት ወዲህ ግንኙነታቸው የመተማመን ችግር አጥልቶበታል። እናም አሁን ቤይጂንግ ስልታዊ ወሳኝ እና ኢ ተገማች የሆነችውን አጋሯ ጋር ያላትን ግንኙነት ዳግም ለመቃኘት እየሞከረች ነው።
ቻይና በድንበሯ መረጋጋትን እና ፒዮንግያንግ ደግሞ ተፅዕኖ ማሳደር ትፈልጋለች።
አገሪቱ ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር መርሃ ግብር ፍላጎት ምክንያት በሚኖረው ቀውስ ተስባ መግባት ግን አትፈልግም።
ስለዚህም የፕሬዝዳንት ዢ የዚህ ሳምንት ጉብኝት ከወዳጅነት ይልቅ የኃይል ተፅዕኖ ላይ የበለጠ ሊያተኩር የሚችለው።
ደቡብ ኮሪያ ዢ በሰሜን ኮሪያ እና በአሜሪካ መካከል ቤጂንግን እንደ አሸማጋይ አድርገው ሊያቀርቡ ይችላል የሚል እምነት ቢኖራትም፤ ቻይና ግን ሌሎች ፍላጎቶች ይኖራት ይሆናል።
የምዕራብ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለቢቢሲ ቻይና እያደገ በመጣው የፒዮንግያንግ እና ሞስኮ ወዳጅነት እንደተጨነቀች ተናግረዋል።
ከሳምንታት በፊት ዢ የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ተቀብለው ካነጋገሩ በኋላ በተለይም ቤይጂንግ በዓለም መድረኮች ያላትን ስፍራ እያሳደገ በመሆኑ፣ የሰሜን ኮሪያውን መሪ ኪም ጆንግ ኡን አደብ መግዛታቸውን ማረጋገጥ ይሻሉ።
ውጥረቱን ማርገብ
በቤይጂንግ እና ፒዮንግያንግ መካከል ያለው ግንኙነት መቀዛቀዙ የተደበቀ ቢመስልም የተሰወረ አልነበረም።
እ.አ.አ ጥቅምት 2024 75ተኛ ዓመት ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የመሠረቱበትን ዓመት አላከበሩም። ለሕዝብ ይፋ የሚሆኑ መልዕክቶችም አልተሰሙም።
ከዚህ አንድ ወር ቀደም ብሎ የቻይና አምባሳደር የሰሜን ኮሪያን የምስረታ በዓል ላይ አልታደሙም። ከሞስኮ ጋር ከነበረው ሞቅ ያለ ግንኙነት አንፃር ባለፉት ዓመታት በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ግንኙነት አልነበረም።
ከሞስኮ ጋር እያደገ ያለው ቀረቤታ ቤይጂንግን አልጣማታም።
ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ ከከፈተች ወዲህ ሰሜን ኮሪያ ከፑቲን ጋር ወታደራዊ ትብብሯን አጠናክራለች።
እ.አ.አ በ2024 ፑቲን ፒዮንግያንግን ሲጎበኙ አገራቱ የጋራ የመከላከያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
2,300 የሚሆኑ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ለሩሲያ ሲዋጉ በዩክሬን እንደተገደሉ የቢቢሲ ምርመራ አረጋግጧል።
ፒዮንግያንግ ለሩሲያ ተተኳሽ በነዳጅ እና እርዳታ ለውጥ በማቅረብ የሞስኮን ጦርነት እያገዘች ነው በሚል ትከሰሳለች። ይህም ዋሽንግተንን እና አጋሮቿን ሲያሳስብ ቻይናንም ኮርኩሯል።
የኒውክሌር ፖሊሲ ባለሙያ የሆኑት አንኪት ፓንዳ "ቻይና በሞስኮ እና ፒዮንግያንግ በፍጥነት ግንኙነታቸው እያደገ ባለበት ወቅት ጥቅሞቿ መከበራቸውን ማረጋገጥ ትፈልጋለች' ይላሉ።
ቻይና አንድ ይፋዊ የመከላከያ ስምምነት ብቻ ያላት ሲሆን፤ ይህንንም ስምምነት ያሰረችው ከሰሜን ኮሪያ ጋር ነው።
ስለዚህም ቤይጂንግ ፒዮንግዮንግ ላይ ሩሲያ ተፅዕኖ ፈጣሪ የምትሆንበትን የቢሆን እይታ የማትቀበለው ለዚህ ነው። መተማመን ያላቸው፤ ጥገኛ ያልሆኑ ኪም ቻይና የኃይል ተፅዕኖ ይቀንሳል ማለት ነው።
ቤይጂንግ ግንኙነቷን ለማደስ በሚመስል መልኩ ምላሽ ሰጥታለች። ባለፈው ዓመት ፕሬዝዳንት ዢ ኪምን በቤጂንግ የወታደራዊ ትርዒት ላይ በመጋበዝ ከፑቲን ጎን እንዲቆሙ አድርገዋል።
ሁለቱ ጎረቤት መሪዎች ከስድስት ዓመታት በኋላ በይፋ ሲገናኙ የመጀመሪያ ነበር።
ዢ ሁለቱን አገራት "መልካም ጎረቤቶች፤ መልካም ወዳጆች እና ከጋራ እጣ ፈንታ ባለፈ መልካም ጓዶች" ሲሉ ያሞገሱ ሲሆን፤ የቅርብ ስልታዊ ቅንጅት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ ይፋዊ መግለጫ ሳይጠቀስ የቀረው የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ነው።
በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ የእስያ ማዕከል ተጋባዥ ባልደረባ የሆኑት ሊ ሲዮንግ-ሀዩን ቤጂንግ በፒዮንግያንግ እና ሞስኮ እያደገ ያለ አጋርነት ዙሪያ "የተደበላለቀ ስሜት" አላት ይላሉ።
በአንድ በኩል አጋርነቱ ዋሽንግተንን ትኩረት በመንፈግ እና ፖሊሲዋ ላይ በርካታ ስጋቶችን በመደቀን የሚያወሳስብ በመሆኑ በተዘዋዋሪ ቻይናን ይጠቅማል ይላሉ።
ነገር ግን በሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ መካከል ወታደራዊ ትብብርን ማሳደግ ከአሜሪካ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ጠንካራ የሦስትዮሽ ወታደራዊ ምላሽ ሊያስነሳ ይችላል በማለት ይህም ቤጂንግን እንደደሚኣሳስብ ጠቅሰዋል።
ቻይና የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር መርሃ ግብር ድጋፏን የማትሰጠው ለዚህ ነው። የአሜሪካ እና አጋሮቿ በቀጣናው ያላቸውን እንቅስቃሴ ያሳድጋል የሚል ስጋት አላት።
ይሁን እንጂ ቻይና ችግሩን ፊት ለፊት እየተጋፈጠች አይደለም።
እ.አ.አ በ2022 አሜሪካ በመንግሥታቱ ድርጅት ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ያደረገችውን ሙከራ ቻይና እና ሩሲያ ድምፅን በድምፅ በመሻር ውድቅ አድርገዋል።
ቻይና በፒዮንግያንግ ኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ ጠንካራ አቋም ብትወስድ "ሰሜን ኮሪያን ወደ ፑቲን እቅፍ ይገፋል" ይላሉ የስትራቴጂክ እና የዓለም አቀፍ ጥናት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ክፍል ፕሬዝዳንት የሆኑት ቪክተር ቻ።
የተግባር አጋር
ኪምም ቢሆኑ ግዙፍ የእርዳታ ምንጩን መግፋትን አይቋቋሙትም።
ባለፈው ዓመት ቻይና ለሰሜን ኮሪያ የላከችው ምርት 2.3 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል። ይህም በስድስት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛው ነው።
ከስድስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ከቤጂንግ ወደ ፒዮንግያንግ የሚወስደው የመንገደኞች ባቡር ባለፈው ዓመት ተጀምሯል።
ተንታኞች ይህንም ፒዮንግያንግን ወደ ቀለበቷ ለመመለስ በቤይጂንግ የተወሰደ ስሌት ነው ይላሉ።
ለኪም የተግባር ምርጫ ነው። የዩክሬን ጦርነት ሲቋጭ ሩሲያ ሰሜን ኮሪያን እርዳታን መፈለጓ ይቀንሳል። እንደተገለሉት ፑቲን ሳይሆን ዢ በቤጂንግ የዓለም መሪዎችን እየተቀበሉ ነው።
ስለዚህም ኪም በደካማ አጋር ላይ ተንጠልጥለው መቅረት አይፈልጉም።
ነገር ግን ይህ ግንኙነት ከጅምሩም ችግር ላይ ነበር።
ኪም ሥልጣናቸውን የተረከቡት ከአባታቸው የተለየ ትኩረት አቅጣጫ ይዘው ነው።
ኪም ጆንግ ኢል በተደጋጋሚ ቻይናን በመጎብኘት እና የቤይጂንግን እርዳታን የተደገፉ ሲሆኑ፤ ልጃቸው ወደ ኒውክሌር ልማት መርሃ ግብራቸው ወዲያው ነበር የተሯሯጡት።
በመጀመሪያ ስድስት ዓመት የሥልጣን ቆይታቸው ኪም 90 ባሌስቲክ ሚሳኤል እና አራት የኒውክሌር ፍንዳታ ሙከራ አድርገዋል። ይህም አባታቸው እና አያታቸው ያደረጉት ሙከራ ጋር ተዳምሮ የሚበልጥ ነው።
ይህ ቤጂንግን አሳስቧታል። በቻይና አረጋጊ መሪ ተደርገው ይታዩ የነበሩት የኪም አጎት ግድያ ግንኙነቱን የበለጠ አሻክሮታል።
ዢ ለዚህ ምላሽ የሰጡት ኪምን ከማግኘታቸው በፊት ደቡብ ኮሪያን በመጎብኘት ደስተኛ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል። ይህ እርምጃ ሆን ተብሎ መዝለል ተደርጎ ታይቷል።
ሰሜን ኮሪያ ቻይናን "ወላዋይ እና ጠላታችን" በማለት ነበር ምላሽ የሰጡት።
በ2018 በኒውክሌር መርሃ ግብራቸው ማዕቀቡ ሲበረታባቸው ኪም የመጀመሪያቸውን የውጭ አገር ጉብኝት አድርገዋል።
የጥይት መከላከያ በተሸፈነው ባቡራቸው ቤይጂንግ አቅንተዋል። ይህ ንግግር ጥንቃቄ የተሞላበት አጋርነት ማስጀመሪያ ሆኗል።
ኪም ከዚህ በኋላ የአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ መሪዎችን አግኝተዋል። ይህም ዘወትር በቻይና ምክር ላይ የተመሰረተ ነው። መልዕክቱ ግልፅ ነው። ፒዮንግያንግ ያለ ቤይጂንግ ድጋፍ አትደራደርም የሚል ነው።
ዛሬ ሰሜን ኮሪያ ለቻይና ጋሻ እና ሸክም ሆና እያገለገለች ነው። የአሜሪካን ኃይሎች በርቀት የምትጠብቁ ቢሆንም የጦር መሣሪያ ሙከራዋ ግን ቀጣናውን አለመረጋጋት ስጋት ውስጥ ጥሎታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኪም የቻይናን ጥበቃ ካለ ቻይና ቁጥጥር ይሻሉ።
ሁሉቱም ወገኖች አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ እምነት የላቸውም። ነገር ግን ለአሁኑ አንዳቸው ሌላኛቸው እንደሚያስፈልጉ እና ለመነጋገር ይህ በቂ ነው ብለው ያምናሉ።