በሕንድ ተማሪዎች ሂጃብ እንዳይለብሱ መከልከሉ ግጭት ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Umesh Marpally
በሕንዷ ካርናታካ ግዛት ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው ትምህርት ቤት መግባት አይችሉም መባሉን ተከትሎ በግዛቷ ግጭት ተቀስቅሷል።
ይህ ውሳኔ በግዛቷ በሂንዱ እና በእስልምና ሃይማኖት ተካታዮች ዘንድ ከፍተኛ ውጥረትን ፈጥሯል።
ሂጃብ መልበስ መከልከሉን ተከትሎ የተነሳው ውጥረት እና ግጭት በሕንድ መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን አሁን ላይ ጉዳዩ የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደርሷል።
የግዛቷን ውሳኔ ተከትሎ በተከሰቱ ግጭቶች በርካቶች የተጎዱ ሲሆን ትምህርት ቤቶችም ለሦስት ተከታታይ ቀናት ዝግ ሆነዋል።
በትምህርት ቤት ሂጃብ የመልበስ መብት አለን የሚሉ ስድስት ሴት ተማሪዎች የበርካቶችን ቀልብ ስበው ቆይተዋል።
የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዋ ማላላ ዮሱፍዛይ ስድስቱ ተማሪዎች ሂጃብ የመልበስ መብት አላቸው በማለት ድጋፏን ገልጻ፤ የግዛቷ አስተዳዳሪዎች ውሳኔን "አስከፊ" ብላዋለች።
'ሂጃብ መልበስ መብት ነው' ብላ አንድ ተማሪ ለፍርድ ቤት ባቀረበችው አቤቱታ ላይ፤ ሂጃብ መልበስ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠ መሠረታዊ የሃይማኖት መብት መሆኑን ተከራክራለች።
ስድስቱ ሴት ተማሪዎች የተቃውሞ ድማጻቸውን ማሰማት የጀመሩት ሂጃብ በመልበሳቸው ወደ መንግሥታዊው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ አትገቡም ተብለው በር ከተዘጋባቸው በኋላ ነው።
በግዛቷ የሚገኙ ሌሎች ተማሪዎች ሂጃብ በመልበሳቸው ምክንያት በትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ ሲደረጉ የሚሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በርካቶችን አስቆጥቷል።
ይህን ውሳኔ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ሲቃወሙት፤ ወግ አጥባቂ የሂንዱ ሃይማኖት ተከታዮች ደግሞ ለውሳኔው ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
ትናንት ማክሰኞ የካቲት 1 በሁለቱ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ግጭት ተከስቶ በርካቶች መጎዳታቸውን የሕንድ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የግዛቷ አስተዳዳሪ ባሳቫራጅ ሞናኢ ትምህርት ቤቶችን ለሦስት ቀናት ከዘጉ በኋላ፤ ተማሪዎች፣ መምህራን እና የትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች ሰላም እና መግባባትን እንዲያሰፍኑ ተማጽነዋል።












