ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና የኔቶን መስፋፋት በመቃወም ከሩሲያ ጎን ነኝ አለች
ቻይና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ወይም የኔቶ መስፋፋትን የተቃወመችውን ሩሲያን እንደምትደግፍ አስታወቀች። ይህም የምዕራቡን ዓለም ግፊት ለመቋቋም በጋራ ለቆሙት አገራቱ ሌላ የአጋርነት ምልክት ሆኗቸዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የክረምት ኦሊምፒክን እያስተናገደች በምትገኘው ቻይና ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት አገራቱ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ስምምነት የሚያንጸባርቅ መግለጫ አውጥተዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን የምዕራቡ ዓለም አገራት የኔቶ ጥምረትን ጦር ሰበብ አርገው ሩሲያን ለማናጋት እየሞከሩ ነው ሲሉ ይከሳሉ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት ከዩክሬን ጋር ውጥረት በተፈጠረበት በዚህ ወቅት ሲሆን ዩክሬንን የመውረር ዕቅድ እንደሌላቸው በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ የሩሲያ ወታደሮች የቀድሞዋ የሶቪየት ግዛት በነበረችው በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ መሰፍራቸው ከምዕራባውያን ጋር ያለው መቃቃርን አካሮታል። ሩሲያ እና ዩክሬን "አንድ አገር ናቸው" ብለው የሚያምኑት ፑቲን ዩክሬን ወደ የኔቶ አባል እንዳትሆን አበክረው እየጠየቁነው።
የፑቲንን የቤይጂንግ ጉበኝትን ተከትሎ የወጣው ረዥሙ የጋራ መግለጫ ዩክሬንን በቀጥታ ባይመለከትም አገራቱ ኔቶ የቀዝቃዛውን ጦርነት ርዕዮተ ዓለምን ያዘለ ነው ሲሉ ተችተዋል።
የሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ምክክር ከክረምቱ ኦሊምፒክ መክፈቻ በፊት የተከወነ ሲሆን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ገጽ ለገጽ ሲገናኙ የትላንቱ የመጀመሪያቸው ነው።
መግለጫው "በሩሲያ እና በቻይና መካከል ያለው ወዳጅነት ገደብ የለሌው እና 'የተከለከለ' የሚባል የስምምነት መስክ የለም" ሲልም አክሏል።
ቻይናና ሩሲያ በተለያዩ የደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ስምምነት አላቸው። ከዚህ ቀደም ሁለቱ አገራት በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና በአውስትራሊያ መካከል የተደረሰው እና 'አውኩስ' የሚል ስያሜ ያለው ወታደራዊ ስምምነት "እጅግ ያሰጋናል" ብለው ነበር።
ከወራት በፊት ይፋ የተደረገው ወታደራዊ ስምምነት አውስትራሊያ በእስያ ፓስፊክ አካባቢ ያለውን ደኅንነት ለማጠናከር በሚል በኒውክሌር ኃይል የሚንቀሳቀሱ የባሕር ሰርጓጅ መርከቦችን እየገነባች ነው።
ታዲያ ስምምነቱ እና ይህ ተግባር በደቡብ ቻይና ባሕር ባሉ አወዛጋቢ ግዛቶች ላይ ውጥረትን አንግሳለች በሚል የሚከሷትን ቻይና ለመመከት የተደረገ ጥረት ተደርጎ ተወስዷል።
በሌላ በኩል ሩሲያ አንድ ቻይና የሚለውን ፖሊሲ እንደምትደግፍ አረጋግጣለች። የአንድ ቻይና ፖሊሲ ከቻይና አስተዳደር ፍጹም የተለየ የራሷ አስተዳደር ያላትን ታይዋን ከጊዜያት በኋላ የቻይና አካል እንድትሆን የሚደግፍ ፖሊሲ ነው።
ሆኖም ታይዋን የራሷ ሕገ መንግሥት እና በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ መሪዎች ያሏት ሲሆን ራሷን ነጻ አገር አድርጋ ትቆጥራለች።