ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፌስቡክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዕለታዊ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር መቀነሱን አስታወቀ
ግዙፉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ፌስ ቡክ በ18 ዓመት ዕድሜው በየዕለቱ ካሉት ንቁ ተጠቃሚዎቹ ቁጥር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅንሽ መመዝገቡን አስታወቀ።
የፌስቡክ ባለቤት የሆነው ካምፓኒ ሜታ እንዳለው ቀደም ሲል 1.930 ቢሊዮን ንቁ ተጠቃሚዎች እንዳሉት የተመዘገበ ሲሆን በጥቅምት፣ ኅዳርና ታኅሣሥ ወራት ግን ይህ አሃዝ ወደ 1.929 ቢሊዮን ዝቅ ብሏል።
ከቲክቶክ እና ከዩቲዩብ በኩል እየገጠመው ካለው ከባድ ፉክክር አንጻርና ማስታወቂያ አቅራቢዎች የሚያወጡትን ገንዘብ ከመቀነሳቸው ጋር ተያይዞ በገቢው ላይም የሚታየው ጭማሪ ዝግ ያለ መሆኑን አመልክቷል።
በተጨማሪም በኒው ዮርክ የአክሲዮን ገበያ ላይ የሜታ የየአክሲዮን ሽያጭ ድርሻ ከ20 በመቶ በላይ አሽቆልቁሏል። ይህም ኩባንያው ካለው የአክስዮን ገበያ ዋጋ ላይ 200 ቢሊዮን ዶላር ያህል ቅናሽ መሆኑ ነው።
ይህ የአክስዮን ድርሻ መቀነስ የታየው በሜታ ላይ ብቻ ሳይሆን ትዊተርን በመሳሰሉ በሌሎችም የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይም ጭምር ነው።
የሜታ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክዛከርበርግ እንዳለው የካምፓኒው የሽያጭ እድገት የቀነሰው ተጠቃሚዎች በተለይ ወጣቶች ወደ ሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ፊታቸውን በማዞራቸው ነው።
የፌስቡክ ባለቤት ካምፓኒ ከቻይናው ቲክቶክ ጋር ለመፎካከር ሲል የቪዲዮ ምስሎችን የሚያቀርብበትን መንገድ ለመጀመር ከፍተኛ ገንዘብ ቢያፈስም የሚጠብቀውን ያህ ገቢ ግን አላስገኘለትም።
ነገር ግን ኩባንያው አሁንም ከኋላው መጥተው ተጠቃሚው የሚፈልገውን አገልግሎት የሚያርቡ ተፎካካሪ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን ለመብለጥ በተለይ በቪዲዮና ሌሎች እጅግ የዘመኑ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ተግቶ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።
ከማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ግዙፍ የሆነው ፌስቡክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቪዲዮ አገልግሎቶችን እየሰጡ ያሉት ቱክቶክና ዩቲዩብ ከፍተኛ ተጠቃሚዎችን እያገኙ ሲሆን በተለይ ወጣቶች እነዚህ መድረኮች ይመርጣሉ።
ይህንንም ፉክክር ለማሸነፍ ፌስቡክ ተጨማሪ አገልግሎቶችን ለማቀረብ ጥረት እያደረገ ነው።