በደቡባዊ አፍሪካ በርካቶችን የገደለው ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን ያሳያል- ተመድ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን በአፍሪካ ደቡባዊ ክፍል የሚገኙ አገራትን የመታውና የበርካታ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን እውነታ ያመላከተ መሆኑን ተናገሩ።
'አና' በተባለውና ነፋስ በቀላቀለው ዝናብ ሳቢያ በደረሰው ጉዳት የሟቾች ቁጥር 86 ደርሷል።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በማዳጋስካር፣ ሞዛምቢክ እና ማላዊ በአደጋው ድልድዮች እና መንገዶች በጎርፍ በመወሰዳቸው መንቀሳቀስ ያልቻሉ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ለመድረስ እየጣሩ ነው።
ባለሥልጣናት በሚቀጥለው ሳምንት 'ባትሲራይ' የተባለው ሁለተኛ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ አህጉሪቷን ይመታ እንደሆነ እየተከታተሉ ይገኛሉ።
በሞዛምቢክ በአደጋው 18 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ 120 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ተጎጂ ሆነዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የህጻናት አድን ድርጅት ( ዩኒሴፍ) ባለሥልጣን ማሪያ ሊዩሳ ፎረናራ "አና የተሰኘው ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ስላለው ተጽዕኖ የሚያሳስብ ነው" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ እና ለመጠበቅ በርካታ ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል።
በሞዛምቢክ ናምፑላ ግዛት አሳ በማስገር የሚተዳደረው አብዱል ኢብራሒም " አሳ የማሰግርበት ጀልባ በኃይለኛው ነፋስ ተወስዶብኛል፤ ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነት ክስተት አይቼ አላውቅም፤ ከደረሰብኝ ጉዳት ለማገገም ለእኔ በጣም አስቸጋሪ ነው" ሲል ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግሯል።
በኃይለኛው ነፋስ ቤቷ የተወሰደባት ማሪያ ጆሴም ከሁለት ልጆቿ ጋር በትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልላ እንደምትገኝ ለዜና ወኪሉ ተናግራለች።
" ምንም የተረፈ ነገር የለኝም፤ ሁሉንም ነገር አጥቻለሁ" ብላለች ማሪያ።
እአአ በ2019 'በሳይክሎን ኢንዳይ' ጉዳት ደርሶባቸው መልሰው የተገነቡ መሠረተ ልማቶችም በድጋሜ ፈርሰዋል።
ሰኞ ዕለት ነፋስ በቀላቀለው ዝናብ በተመታችው የመጀመሪያዋ አገር ማዳጋስካር የሟቾች ቁጥር 48 የደረሰ ሲሆን 72 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች መኖሪያ ቤታቸውን እንዳጡ ተዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የማላዊ ፕሬዚደንት ላዛረስ ቻክዌራ በአገሪቷ 20 ሰዎችን የገደለውን ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።
የአደጋ መከላከልና ስጋት አመራር ኤጀንሲ በአደጋው ሳቢያ መንገዶች በመፈራረሳቸው ቤተሰቦች የሟች ቤተሰብ አባላቸውን አስክሬን ለመቅበር ተሸክመው ለመሄድ መገደዳቸውን ገልጿል።
በአገሪቷ ደቡባዊ ግዛት የምትገኘው ቺክዋዋ ከተማ ነዋሪዎች ጎርፉ እስከሚያልፍ ለሁለት ቀን በዛፍ ላይ ተንጠልጥለው እንዴት እንዳሳለፉ አስረድተዋል።
የአየር ንብረት ባለሥልጣናት ከሕንድ ውቅያኖስ ተነስቶ ወደ ምዕራብ እየገሰገሰ ያለውንና 'ባትሲራይ' የተባለውን አውሎ ነፋስ በቅርበት እየተከታተሉ ነው።












