ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ በምኩራብ ታግተው የቆዩ ግለሰቦች ነፃ ወጡ
በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ዳላስ ውስጥ በሚገኝ የአይሁዳውያን እምነት ተከታዮች ማምለኪያ፣ ምኩራብ ውስጥ ታግተው የነበሩት አራቱ ሰዎች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው መለቀቃቸው ተሰምቷል።
ፖሊስ ለተከታታይ አስር ሰአታት ከበባ አድርጎ ሲጠባበቅ ነበር።
ሰዎቹ የታገቱት ቅዳሜ ዕለት የጠዋት አምልኮ ፕሮግራም በመታደም ላይ ሳሉ ነበር ተብሏል።
ፖሊስ ወዲያው ልዩ ቡድኖችን ወደ ቦታው በመላክ ነገሮችን ለማረጋጋት የሞከረ ሲሆን የአሜሪካ ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይም ቢሆን በተደራዳሪዎቹ በኩል ከአጋቹ ጋር ለሰአታት ሲወያዩ ነበር።
የአጋች ታጋች ድራማው ከመጠናቀቁ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት ፍንዳታና የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር። አጋቹ በዚህ መሀል መሞቱን ፖሊስ አስታውቋል።
በምኩራቡ ከታገቱት አራት ሰዎች መካከል አንደኛው የሃይማኖት አባት መሆናቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።
አጋቹ ድንገት ገብቶ ሰዎችን ሲያስፈራራ የአምልኮ ስነስርአቱ በበይነ መረብ አማካይነት በቀጥታ እየተላለፈ ነበር።
ከታጋቾቹ መካከል የመጀመሪያው ግለሰብ ከስድስት ሰአታት በኋላ ምንም ጉዳት ሳይደርስበት የተለቀቀ ሲሆን ቀሪዎቹ ሶስት ሰዎች ደግሞ ከሰአታት በኋላ በፖሊስ ታጅበው ሲወጡ ታይተዋል።
ምንም እንኳን ታጋቾቹን ለማዳን የተመደበው ልዩ የፖሊስ ቡድን ወደ ቅጥር ግቢው ሰብሮ የገባ ቢሆንም አጋቹ በምን አይነት ሁኔታ ህይወቱ እንዳለፈች ግን የታወቀ ነገር የለም።
አጋቹ ወደ አምልኮ ቦታው መግባቱ ሲሰማ ወዲያውኑ ፖሊስ በአካባቢው እንዲደርስ የተደረገ ሲሆን በቦታው የነበሩ ሌሎች ሰዎች እንዲርቁም ተደርጓል።
በቀጥታ ስርጭት ሲተላለፍ በነበረው የአምልኮ ስነስርአት ላይ አንድ ግለሰብ ገብቶ ድምጹን ከፍ አድርጎ ሲናገር ይታያል። በቪዲዮውም ላይ '' እህቴን በስልክ አገናኙኘን፤ እኔስ መሞቴ አይቀርም'' ሲል ይሰማል።
ከዚህ በተጨማሪም ''አሜሪካ ውስጥ የሆነ ችግር አለ'' ሲል ተደምጧል። ከዚህ በኋላ የቀጥታ ስርጭቱ ወዲያው ተቋርጧል።
አጋቹ በቪዲዮው ላይ ፓኪስታናዊው ኒውሮሳይንቲስት አፊያ ሲዲቂ ከእስር እንዲፈታ ጠይቋል። እንዲለቀቅ የተጠየቀው ግለሰብ የአሜሪካ ወታደሮችን አፍጋኒስታን ውስጥ ለመግደል በመሞከር ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ 86 ዓመት ተፈርዶበት በእስር ላይ ነው የሚገኘው።
ቤሪ ክሎምፑስ የተባሉት ግለሰብ የአምልኮ ቦታው በአውሮፓውያኑ 1999 ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ አባል እንደነበሩ የገለጹ ሲሆን አንድ ሌላ ጓደኛቸው ስለተፈጠረው ነገር ነግሯቸው የቀጥታ ስርጭቱ እስከሚቋረጥ ድረስ ሲከታተሉ እንደነበር ገልጸዋል።
''የሚሆነውን ነገር ማየትና መስማት በጣም ይከብድ ነበር። ምን ሊፈጠር እንደሚችል አለማወቅና ምንም ማድረግ አለመቻል በጣም ያስፈራል'' ሲሉ ለሬውተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።