ኮቪድ-19፡ በእንግሊዝ በኦሚክሮን ቫይረስ በርካታ ህጻናት ሆስፒታል መግባታቸው ተገለጸ

ታትሟል

በእንግሊዝ ከታኅሣሥ ወር ወዲህ በርካታ ህጻናት በኮቪድ-19 ተይዘው ሆስፒታል የገቡ ሲሆን ለከፋ ህመም አለመዳረጋቸውን የዩናይትድ ኪንግደም ባለሙያዎች ገለጹ።

በህጻናቱ ላይ የታየው የመጀመሪያ ውጤት የሚያበረታታ መሆኑንም ሐኪሞች የገለጹ ሲሆን "ኮቪድ የሚያስከትለው አደጋ ዝቅተኛ ሆኗል" ብለዋል።

ህጻናት ህክምና ካስፈለጋቸው የአገሪቷ የጤና አገልግሎት በቂ ቦታ አለው ሲሉም ወላጆች እንዲረጋጉ ሐኪሞቹ መክረዋል።

በቫይረሱ ተይዘው ሆስፒታል የገቡት አብዛኞቹ ህጻናት ከሳል ጋር አሊያም ያለሳል ትኩሳት የነበራቸው ሲሆን ጥቂቶቹ ግን እንደ ኦክስጅን ያሉ ሕክምና አስፈልጓቸው ነበር።

ሆስፒታሎች ሲከታተሏቸው የነበሩ ህጻናት አብዛኞቹ ከ5 ዓመት በታች ያሉ፣ በተለይም ደግሞ ከአንድ ዓመት በታች የሆኑ ናቸው።

የእንግሊዝ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) በ33 ሆስፒታሎች ውስጥ በሚገኙ እና በኦሚክሮን በተያዙ 50 የሚሆኑ ህጻናት ላይ የዳሰሳ ጥናት ያደረገ ሲሆን አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ህጻናት በመኖራቸው መረጃ ማሰባሰቡን አሁንም ቀጥሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የድንገተኛ አደጋ ሳይንሳዊ አማካሪ ቡድን (ሴጅ) በኦሚክሮን የተያዙ 171 ህጻናትን አዲሱ ወረርሽኝ ከመከሰቱ ቀደም ብሎ ከነበሩት ጋር በማነጻጸር አንድ ሪፖርት አውጥቷል።

ሴጅ ባወጣው ሪፖርት አሁን ላይ እየተዛመተ ባለው ቫይረስ ህጻናት የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን አመልክቷል።

አሁን ላይ 4.3 ሚሊየን የሚጠጋ ሕዝብ ወይም ከ15 ሰዎች አንዱ በኮቪድ-19 እንደሚያዝ ይታሰባል።

እድሜያቸው ከ20 አስከ 29 የሚደርሱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ከፍተኛ ሲሆን ከ80 ዓመት በላይ የሆኑ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ግን ዝቅተኛ መሆኑን ሪፖርቱ ገልጿል።

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ከዚህ ቀደም በነበረው ወረርሽኝ ወቅት በኮቪድ-19 የሚያዙ ህጻናት አይታመሙም ነበር፤ ቢታመሙም ቁጥራቸው ዝቅተኛ ነው። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በሌላ ህመም ሳቢያ ሆስፒታል ገብተው እዚያው እያሉ በኮቪድ የተያዙ ናቸው።

በድንገተኛ ህክምና ሳይንሳዊ አማካሪ ቡድን ውስጥ መንግሥትን የሚያማክሩት ፕሮፌሰር ካሉም ሰምፕል "ጥናታችን ባለፉት አራት ሳምንታት ከኦሚክሮን ጋር በተያያዘ ሆስፒታል የሚገቡ ህጻናት በተለይም ከአንድ ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ቁጥር መጨመሩን አሳይቷል" ብለዋል።

"በሚገርም ሁኔታ አሁን እያየን ያለነው ከ42 በመቶ በታች ያሉ ህጻናት እድሜያቸው ከአንድ ዓመት በታች ነው፤ ቀደም ብሎ ግን ይህ አሃዝ 30 በመቶ ነበር" ሲሉም ፕሮፌሰሩ አክለዋል።

በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የህጻናት ጤና ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ሩስል ቫይነር ኮቪድ-19 በህጻናት ላይ እንደተለመደው የክረምት ጉንፋን ዓይነት ባህርይ እያሳየ ነበር።

በሕክምና ዕይታ ይህ በጣም የሚያረጋጋ ሲሆን ግማሾቹ ህጻናት ሆስፒታል የገቡት ለመታየት ብቻ ነው። በሆስፒታል የቆዩበት አማካይ ጊዜም ዝቅተኛ ነው። ሁለት ቀናት ገደማ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ሌሎች ውስብስብ የጤና ችግሮች ያሉባቸው ህጻናትም በቫይረሱ ሳቢያ ለከፋ ህመም አልተዳረጉም።

ህጻናትና ጨቅላ ህጻናት የሚያሳዩት የኮቪድ-19 ምልክት ትኩሳትና ቀላል ሳል ነው።

ይሁን እንጂ ወላጆች አሊያም ተንከባካቢዎች ልጆቻቸው ትኩሳት ሲያጋጥማቸው የህክምና ባለሙያ ማማከር ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህም ባሻገር ነፍሰ ጡር እናቶች የኮቪድ ክትባትን በመውሰድ እራሳቸውንም ሆነ ልጆቻቸውን ከቫይረሱ መከላከል ይችላሉ።

ያልተከተቡ እናቶች በእርግዝናቸው የመጨረሻ ወር በቫይረሱ ከተያዙ ያለጊዜ መውለድንና በማህጸን ውስጥ የህጻን ሞትን ጨምሮ ከእርግዝና ጋር ለተያያዙ ውስብስብ የጤና ችግሮች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው።

በህጻናት ላይ ስለሚያጋጥም ትኩሳት

የህጻናትን የትኩሳት መጠን በትክክል እና በፍጥነት ለማወቅ ዲጂታል የሙቀት መለኪያ (ቴርሞሜትር) መጠቀም ያስፈልጋል።

ትኩሳት የሚባለውም 38 ሴልሺየስ ወይም ከዚያ በላይ ሲሆን ነው። ይህ የሙቀት መጠን የኮቪድ እና ሌሎች ኢንፌክሽኖች ምልክት ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ የሕክምና ባለሙያ ማማከር አስፈላጊ ነው።