የሳዑዲ ፍርድ ቤት በፆታዊ ትንኮሳ ጥፋተኛ የተባለውን ሰው ለመጀመሪያ ግዜ በይፋ እንዲቀጣ አዘዘ

ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በሳዑዲ በጾታዊ ትንኮሳ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ሰዎች እስከ ሁለት ዓመት እስራት እና እስከ 27 ሺህ ዶላር የሚደርስ ቅጣት ይጣልባቸዋል።
ታትሟል

የሳዑዲ አረቢያ ፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ በፆታዊ ትንኮሳ ጥፋተኛ የተባለውን ግለሰብ በይፋ ስሙ እንዲጠራ መወሰኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

ያሲር አል አራዊን የተባለው ግለሰብ አንዲትን ሴት ጸያፍ ቃላትን በመጠቀም በማዋከቡ ነው በመዲና ከተማ በሚገኘው የወንጀል ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ያስባለው።

የስምንት ወር እስራት እና 1 ሺህ 330 ዶላር [ 65 ሺህ ብር] የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበታል።

የፀረ-ትንኮሳ ሕጉ ከአንድ ዓመት በፊት የተሻሻለ ሲሆን የወንጀለኞችን ስም እና የቅጣት ውሳኔ በአገር ውስጥ ጋዜጦች በራሳቸው በጥፋተኞቹ ወጪ እንዲታተም የሚያደርግ ነው።

ዳኞች "የወንጀሉ ክብደት እና በኅብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ" በመመርመር ለእንዲህ ዓይነቱ ቅጣት ያበቃል አያበቃም የሚለውን የመወሰን ሥልጣኑ ተሰጥቷቸዋል።

ማሻሻያው በወቅቱ በወግ አጥባቂ የባህረ ሰላጤው አገራት ውስጥ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘ ሲሆን አንድ አስተያየት ሰጪ "እጅግ የዘገየ" ሲሉ ገልጸውት ነበር።

እ.ኤ.አ. በ2018 ተግባራዊ የሆነው ሕጉ በጾታዊ ትንኮሳ ጥፋተኛ ሆነው ለተገኙ ሰዎች እስከ ሁለት ዓመት እስራት እና እስከ 27 ሺህ ዶላር የሚደርስ ቅጣት ያስቀምጣል። ተደጋጋሚ ወንጀለኞች እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ እስራት እና እስከ 80 ሺህ ዶላር የሚደርስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

እነዚህ ሕጋዊ እርምጃዎች ቢኖሩም አንዳንድ የሳዑዲ ሴቶች ባለሥልጣናት አሁንም የሚደርስባቸውን ትንኮሳ ለማስቆም በቂ ጥረት እያደረጉ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን ያሰማሉ።

በቅርቡ ለቢቢሲ ሃሳባቸውን ያጋሩ አንድ ግለሰብ እንዳሉት ጾታዊ ትንኮሳዎችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ተቀርጸው በኢንተርኔት ላይ በሚቀርቡበት ጊዜ የሚሰጡ አስተያየቶች በአብዛኛው ሴቶችን ልክ እንደአጥቂዎች ሁሉ የሚወቅስ መሆኑን እንዲሁም ተጎጂዎች እንደ ወንጀለኞች ሁሉ የሚቀጡበት ነው።