ሰሜን ኮሪያ ኪም አዲስ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል አስወነጨፍኩ አለች

ኪም ጆንግ ኡን ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር አዲሱን የሚሳይል ሙከራ ሲመለከቱ

የፎቶው ባለመብት, KCNA/REUTERS

የምስሉ መግለጫ, የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ኪም ጆንግ ኡን አዲሱን የሚሳይል ሙከራ ሲመለከቱ የሚያሳይ ምሥል አትመዋል
ታትሟል

ሰሜን ኮሪያ በመሪዋ ኪም ጆን ኡን አስተዳደር ሥር ሌላ እጅግ ፈጣን ሚሳኤል ሙከራ ማድረጓን አስታወቀች።

የመንግሥት የዜና ወኪል ኬሲኤንኤ እንዳለው ማክሰኞ ዕለት የተተኮሰው ሚሳኤል 1000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ኢላማ 'በትክክል መትቷል'።

ይህ ሰሜን ኮሪያ እንዳስወነጨፈችው በይፋ የተነገረው ሦስተኛው የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ሙከራ ነው።

ሃይፐርሶኒክ ሚሳይል ከባልስቲክ ሚሳይል በበለጠ ለረዥም ጊዜ መወንጨፉ ሳይታወቅ መጓዝ ይችላል።

ሁለቱ ሙከራዎች የተደረጉት ኪም ጆንግ ኡን የፒዮንግያንግን መከላከያ ለማጠናከር በአዲስ ዓመት ባደረጉት ንግግር ላይ ቃል ከገቡ በኋላ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው።

ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ማክሰኞ እለት የተደረገውን ሙከራ መለየት የቻሉ ሲሆን 'ከሰሜን ኮሪያ ወደ ባህር ሚሳኤል ተተኩሷል' ብለዋል።

ኬሲኤንኤ የዜና ወኪል በኋላ ላይ "የላቀ የመወንጨፍ አቅም ያለው" ሲል የገለጸው ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል መሆኑን ገልጿል።

ሰሜን ኮሪያ ቀደም ብሎ በአውሮፓውያኑ ጥር 5 ቀን የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ሙከራን በተሳካ ሁኔታ ማድረጓን አስታውቃለች። ይሁን እንጂ ድርጊቷ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን ጨምሮ ከሌሎች አገራት ውግዘት አስከትሎባታል። አገራቱ ፒዮንግያንግ "አለመረጋጋት ከሚያስከትለው ተግባሯ" እንድትታቀብ አሳስበዋል።

ሃይፐርሶኒክ ከባልስቲክ ሚሳኤል ይልቅ ብዙውን ጊዜ ወደ ኢላማው የሚጓዘው በዝቅተኛ ከፍታ ሲሆን ከድምጽ ፍጥነት አምስት እጥፍ በላቀ ሁኔታ መምዘግዘግ ይችላል። ይህም 6 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር በሰዓት እንደማለት ነው።

ሰሜን ኮሪያ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ለማበልጸግ ሙከራ ለማድረግ አሜሪካን እና ቻይናን ጨምሮ የተወሰኑ አገራትን ተቀላቅላለች።

በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተጋሩት ምሥሎች ኪም ጆንግ ኡን ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር ሆነው የሚሳኤሉን ሙከራ ሲመለከቱ አሳይተዋል። ይህም ከመጋቢት ወር 2020 በኋላ ኪም በይፋ ሚሳይል ሙከራ ላይ ሲገኙ ይህ የመጀመሪያቸው መሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል።

ሰሜን ኮሪያን የሚከታተለው የኮሪያ የአደጋ ስጋት ቡድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቻድ ኦካሮል "ምን አልባት ኪም መጀመሪያ ላይ ሌሎች ሙከራዎችን ይፋዊ ባልሆነ መልኩ ተመልከተው ሊሆን ይችላል፤ አሁን ላይ ግን በይፋ መገኘታቸውና በሰሜን ኮሪያ ጋዜጣ ሮዶንግ ሲንሙን ላይ የፊት ገጽ ላይ መውጣታቸው አስፈላጊ ነው" ሲሉ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ይህ ማለት ኪም ከዋና አዲስ ቴክኖሎጂ ሙከራዎች ጋር ተያይዞ በግል መነሳታቸው አያሳስባቸውም ማለት ነው ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለዋል።