ሰሜን ኮሪያ በቀናት ልዩነት በድጋሚ ሚሳኤል ተኩሳለች ተብሎ ተጠረጠረ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሰሜን ኮሪያ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ነው ያለችውን ሚሳኤል ካስወነጨፈች ሳምንትም ሳይሞላ ባሌስቲክ ሚሳኤል ነው ተብሎ የተጠረጠረ ሙከራ አደረገች።
ደቡብ ኮሪያ ማክሰኞ ጠዋት ሚሳኤሉ መተኮሱን እንደደረሰችበት ተናግራለች።
የጃፓን የባህር ጠረፍ ጠባቂዎችም ሰሜን ኮሪያ "ባለስቲክ ሚሳኤል መሰል ነገር" መተኮሷን ገልጸዋል።
ይህ የሆነው ሰሜን ኮሪያ "አለመረጋጋትን ከሚፈጥረው ተግባሯ" እንድትታቀብ የሚያሳስብ መግለጫ ስድስት ሃገራት ካወጡ በኋላ ነው።
"የእኛ ጦር የሚጠረጥረው ከሰሜን ኮሪያ መሬት ወደ ምስራቅ ባህር የተተኮሰ ባለስቲክ ሚሳኤል አግኝቷል" ሲሉ የደቡብ ኮሪያ ዋና አዛዥ ገልጸዋል። የደቡብ ኮሪያ እና የአሜሪካ የደህንነት ባለስልጣናት ዝርዝር ጥናት በማካሄድ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የአሁኑ የሚሳኤል ሙከራ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡን በታህሳስ ወር ባደረጉት ስብሰባ ላይ እንደተገለጸው በ2022 ቅድሚያ ከሚሰጣቸው መካከል የሃገሪቱን መከላከያ ለማጠናከር የገቡትን ቃል አጽንኦት ይሰጣል።
ሰኞ ዕለት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ ተወካይ ከፈረንሳይ፣ አየርላንድ፣ ጃፓን፣ እንግሊዝ እና አልባኒያ ጋር በመሆን ባለፈው ሳምንት የተደረገውን ሙከራ በማውገዝ የጋራ መግለጫ አውጥቷል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ "እርምጃዎቹ የተሳሳተ ስሌት እና የመስፋፋት አደጋን ይጨምራሉ። ለአካባቢው መረጋጋትም ትልቅ ስጋት ይፈጥራሉ" ብለዋል።
ሰሜን ኮሪያን "ከተጨማሪ አከባቢውን ወደ አለመረጋጋት ከሚወስዱ እርምጃዎች እንድትቆጠብ ጠይቀዋል። የጋራ ግብ ወደ ሆነው ኒውክሌር የሌለበትን አካባቢን ለመፍጠር ትርጉም ያለው ውይይት እንድታደርግ" ቡድኑ ጠይቋል።
የአሁኖቹ የሚሳኤል ሙከራዎች ፒዮንግያንግ ኢኮኖሚዋን ክፉኛ በጎዳው የኮሮና ቫይረስ እገዳ ምክንያት የምግብ እጥረት ባጋጠማት ወቅት የተደረገ ነው።
በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት የገዥው ፓርቲ ስብሰባ ላይ ኪም ሃገሪቱ "የመኖር እና አለመኖር ትግል" እየተጋፈጠች ነው ብለዋል። ልማት እና የህዝብን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ከዘንድሮ ግቦች መካከል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣናት ቀደም ሲል በሰሜን ኮሪያ ህጻናት እና አረጋውያን ለረሃብ ተጋልጠዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማበልጸጓን እንድታቆም እየጠየቀች ነው። ፒዮንግያንግ ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ጋር ያላት ግንኙነትም በውጥረት የተሞላ ነው።
ሰሜን ኮሪያ በወታደራዊ እንቅስቃሴዋ ሁለት ገጽታ እያሳየች ነው ስትል ደቡብ ኮሪያ ደጋግማ ትከሳለች።
የሰሜን ኮሪያን "ትንኮሳዎች" ለመከላከል ያስፈልጋል ያለችውን ባህር ሰርጓጅ ባለስቲክ ሚሳኤል ደቡብ ኮሪያ በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሞክራለች።












