ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኮቪድ ምክንያት 11 ተጫዋቾች እንኳን ቢቀሩ ጨዋታ እንደማይሰረዝ ካፍ ገለጸ
በአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፉ ሃገራት የኮቪድ1-9 ወረርሽኝ ቢያጋጥማቸውና 11 ተጫዋች ብቻ ቢቀራቸው እንኳ ጨዋታው እንደማይሰረዝ ካፍ ገልጿል።
የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪው ካፍ ከአስራ አንዱ ተጫዋቾች አንዱም ግብ ጠባቂ ባይሆን ጨዋታው እንደማይሰረዝ አስታውቋል።
ይህንን ማሟላት የማይችል ቡድን በተለምዶ ፎርፌ በሚባለው ሕግ መሠረት የ2-0 ሽንፈት ይጣልበታል ይላል ካፍ።
ካፍ ይህንን ትዕዛዝ ያስተላለፈው ዛሬ ምሽት [እሑድ] ከሚጀምረው ውድድር በፊት በርካታ ሃገራት ተጫዋቾቻችን በኮቪድ ተይዘዋል ብለው ካማረሩ በኋላ ነው።
ካፍ አክሎም "ለየት ያለ ምክንያት" ላላቸው ሃገራት የውድድሩ አጋጅ ኮሚቴ "አስፈላጊውን ውሳኔ ይሰጣል" ብሏል።
ከሁሉም ቀድማ ካሜሩን የገባችው ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት የተወሰኑ ተጫዋቾቿ በኮቪድ ተይዘውባት እንደነበር ሶከር ኢትዮጵያ ዘግቦ ነበር።
ተጫዋቾችን ጨምሮ የአሠልጣኝ ቡድን አባላት በኮቪድ ተይዘው ለቀናት ካገገሙ በኋላ መመለሳቸውን ድረ-ገፁ ዘግቧል።
ባለፈው አርብ ወደ ካሜሩን ማቅናት የነበረባት ግብፅ በኮቪድ ምክንያት ወደ አዘጋጇ ሃገር የምታደርገውን በረራ አራዝማ ነበር።
አልፎም የግብፅ ብሔራዊ ቡድን በኮሮናቫይረስ ምክንያት ልምምድ አለመሥራቱም ተሰምቷል።
ዘጠኝ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን በማንሳት ክብረ ወሰን የጨበጡት ፈርዖኖቹ ቅዳሜ ዕለት ወደ ካሜሩን መብረራቸው ተሰምቷል።
የአርሰናሉ አጥቂ ፒዬር-ኤሜሪክ ኦባሜያንግ በኮቪድ ከተያዙ ሁሉት የጋቦን ብሔራዊ ቡድን አባላት መካከል አንዱ ሆኗል።
ጊኒ ደግሞ ተከላካዩ ሚካኤል ድሬስታምን፣ አማካዩ ሞርላዬ ሲላን እንዲሁም አጥቂው ሶማን ሩዋንዳ ጥላ ነው ወደ ካሜሩን ያቀናችው።
ኬፕ ቨርድና ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የምትሳተፈው ጋምቢያ ባለፈው ሳምንት በርካታ ተጫዋቾቻቸው በኮቪድ መያዛቸውን ይፋ አድርገው ነበር።
ቱኒዚያም እንዲሁም የተወሰኑ ተጫዋቾቿ በኮቪድ መጠቃታቸውን አሳውቃለች።
ዛሬ ምሽት የሚጀምረው የአፍሪካ ዋንጫ በመጀመሪያው ጨዋታ አዘጋጇ ካሜሩን ከቡርኪና ፋሶ ሲያፋልም በሁለተኛው ጨዋታ ኢትዮጵያ ከኬፕ ቨርድ ትገጥማለች።