ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኮሎራዶ የተከሰተው ሰደድ እሳት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን አፈናቀለ
በአሜሪካ ኮሎራዶ ግዛት ውስጥ የሰደድ እሳት መከሰቱን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የተፈናቀሉ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ወድመዋል።
በዴንቨር ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘው ቦልደር ግዛት ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ያለው ሰደድ እሳት ሞት እና የአካል ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።
በሉዊቪል እና ሱፐርየር ከተሞች ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በያዝነው ሐሙስ ዕለት ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ተነግሯቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በግዛቲቷ ውስጥ በአስተዳዳሪው ጃሬድ ፖሊስ አማካኝነት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።
"ንፋሱ ቀዝ ቀዝ ይላል፣ አየሩም ይለዋወጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ያሉት አስተዳደሪው አክለውም "ነገር ግን በዚህ ሰደድ እሳት ለተጠቃችሁ ሁሉ ብቻችሁን እንዳልሆናችሁ ማወቅ ይገባችኋል" ብለዋል።
ታሪካዊ በተባለው ድርቅ ምክንያት በአካባቢው ንፋስ በከፍተኛ ፍጥነት በሚባል በሰዓት 169 ኪሎ ሜትር እየነፈሰ አካባቢውንም እያቃጠለ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም በኮሎራዶ የተከሰቱት የእሳት ቃጠሎዎች በገጠር አካባቢዎች የነበሩ ቢሆንም የቅርብ ጊዜ ቃጠሎዎች ግን በከተማው በተለይም ሃብታም በሆኑ የመኖሪያ ስፍራዎች አካባቢዎች መከሰታቸው ሪፖርት ተደርጓል።
የኤሌክትሪክ መስመሮች በከባዱ ነፋስ መመታቸውንም ተከትሎም አንዳንዶቹ በእሳቱ ላይ የሰደድ እሳቱን በማቀጣጠል ያባባሱ ሲሆን በዘመናዊውም የግዛት ታሪክም ውስጥ አጥፊ በሚል ተመዝግቧል።
የቦልደር ግዛት ፖሊስ ኃላፊ ጆ ፔሌ እንደተናገሩት 370 የሚሆኑ ቤቶች በምዕራብ ሱፐሪየር እንዲሁም በቀድሞው ሱፐሪየር አካባቢ ደግሞ 210 ቤቶች ተቃጥለው ወድመዋል።
በዚህ ቃጠሎ የመገበያያ መደብር እና ሆቴል ሙሉ በሙሉ በእሳቱ ተውጠው መውደማቸው ተነግሯል።
የፖሊስ ኃላፊው አክለው እንዳስረዱት አንድ የአደጋ ሰራተኛና ሌሎች ስድስት ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን ሌሎች ተጨማሪ ጉዳቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ኮሎራዶ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከባድ ድርቅ እያጋጠማት ይገኛል። የአየር ንብረት ለውጥ ለሰደድ እሳት አመች የሆነውን ሞቃታማና ደረቅ የአየር ሁኔታዎችን በመፍጠር ላይ ይገኛል።
የኢንዱስትሪው ዘመን ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አለም በ1.2 ሴንቲ ግሬድ ገደማ እየሞቀች የምትገኝ ስትሆን የአለም መንግስታት ከፍተኛ የሆነ የልቀት መጠን ቅነሳ ካላደረጉ በስተቀር የሙቀት መጠኑ እየጨመረ እንደሚሄድም ተገልጿል።