የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚመለሱ አስታወቀ

ቦይንግ 878

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

ታትሟል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹን ከአንድ ወር በኋላ ወደ በረራ ለመመለስ በመጨረሻው የዝግጅት ደረጃ ላይ መሆኑን አስታወቀ።

ከአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉትን ዘመናዊዎቹን ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹን ከበረራ ውጪ ካደረገ ሁለት ዓመት አልፎታል።

መጋቢት 01 ቀን 2011 ዓ.ም ጠዋት ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ 149 ሰዎችን ይዞ ይበር የነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር ET302 መከስከሱን ተከትሎ ነበር አውሮፕላኖቹ ከበረራ ውጪ የሆኑት።

ይህንን አደጋ ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ካለባቸው የደኅንነት መቆጣጠሪያ ችግር ጋር በተያያዘ በረራ እንዲያቆሙ ተደርገው ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረማሪያምን ጠቅሶ ባወጣው መግለጫ ላይ አየር መንገዱ ከሁሉም በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ለደኅንነት መሆኑን በመግለጽ አውሮፕላኖቹ ወደ አገልግሎት ሊመለሱ መሆናቸውን አመልክቷል።

አየር መንገዱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በዓለም ዙሪያ ያሉ የበረራ ደኅንነት ተቆጣጠሪ አካላት ቦይንግ 737 ማክስ ለበረራ ብቁ ነው ብለው አስፈላጊውን ፈቃድ ከመስጠታቸው በተጨማሪ "በዓለም ዙሪያ ያሉ ሌሎች 34 አየር መንገዶች አውሮፕላኑን ወደ በረራ መመለሳቸውን ተከትሎ ነው" ብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኑን ወደ ሥራ ለመመለስ ሁለት ዓመት ለሚሆን ጊዜ በአውሮፕላኑ ላይ የተደረጉ የዲዛይን ማሻሻያዎችን ሲፈትሽ እና ጥብቅ በሆነ የፈቃድ ሂደት ውስጥ እስኪያልፍ ድረስ መጠበቁን አመልክቷል።

በተጨማሪም የአየር መንገዱ አብራሪዎች፣ መሐንዲሶች፣ ቴክኒሻኖችና የበረራ ሠራተኞች በሙሉ በአውሮፕላኖቹ ደኅንነት ላይ ያላቸው መተማመን አስፈላጊው ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጿል።

ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ባለፈው አንድ ዓመት መንገደኞችን በማጓጓዝ 275,000 የንግድ በረራዎችን ማድረጋቸውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላኖቹ ደኅንነት አስተማማኝ ሆኖ ወደ በረራ ለመመለስ ሁሉም 737 ማክስ አውሮፕላኖቹ ላይ አስፈላጊው ሥራ መከናወኑን ገልጿል።

ይህንንም መሠረት በማድረግ በየካቲት ወር አውሮፕላኖቹን ወደ ሥራ የሚመልስ ሲሆን ከዚያ በፊት በጥር ወር ላይ ስለ ሂደቱ ዝርዝር ማብራሪያ ይሰጣል ብሏል።

ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን እጅግ ዘመናዊ የሚባል ሲሆን በበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓቱ ላይ በነበረ ችግር ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢንዶኔዢያ ላየን ኤር አውሮፕላኖች ተመሳሳይ አደጋ አጋጥሟቸዋል።

በሁለቱ አደጋዎች በአውሮፕላኖቹ ውስጥ የነበሩ ሁሉም 346 ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ቦይንግ ለሟቾቹ ቤተሰቦች በቢሊዮን የሚቆጠር ካሳ እንዲከፍል ተጠይቋል።

ግዙፉ የአውሮፕላኑ አምራች ኩባንያ ቦይንግ በተለይ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ያጋጠመውን አደጋ ተከትሎ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የገባ ሲሆን በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገቢንም አጥቷል።