ኢኳዶር ለሁሉም ዜጎቿ የኮቪድ-19 ክትባትን መውሰድ ግዴታ አደረገች

ታትሟል

ኢኳዶር እየተባበሰ የመጣውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመግታትና እንደ ኦሚክሮን ያሉ ዝርያዎችን ጉዳት ለመቀነስ በሚል አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል የኮቪድ-19 ክትባት እንዲወድ የሚያስገድድ መመሪያ አወጣች።

የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር እንዳለው አጠቃላይ ሕዝቡን ለመከተብ የሚያስችል የክትባት ክምችት ያለ ሲሆን፣ የሕክምና ማስረጃ ያላቸው ሰዎች ብቻ ያለመከተብ መብት ይኖራቸዋል።

ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ውስጥም ማንኛውም ዕድሜው ከአምስት ዓመት በላይ የሆነ ሰው በሙሉ ክትባቱን ይወስዳል ተብሏል።

እስካሁን ድረስ ዕድሜያቸው ለክትባት ከደረሱ ሰዎች ውስጥ 77.2 በመቶ ያህሉ ሁለት ዙር ክትባት ሲወስዱ ከ900 ሺህ በላይ የሚሆኑት ሰዎች ሦስተኛ ዙር ክትባታቸውን ወስደዋል።

የጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው፤ ክትባቱ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችል አቅም የፈጠረና ይህም በቫይረሱ ተይዘው ወደ ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎችን ቁጥር እና ሞትን ለመቀነስ ያገዘ ነው።

በአገሪቱ ሕገ መንግሥት የተቀመጠው የዜጎችን ጤንነት የማስጠበቅ ግዴታ በመንግሥት ጫንቃ ላይ የወደቀ መሆኑንና እርሱን ለማስፈጸም ሕጉን መሠረት ተደርጎ የተሰጠ ውሳኔ መሆኑን የኢኳዶር ጤና ሚኒስቴሩ ገልጿል።

አውስትራሊያ እና ጀርመን ተመሳሳይ ውሳኔ የመስጠት ዕቅድ ያላቸው አገራት ናቸው።

ኢኳዶር ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ ጥቅም ላይ የሚውል የክትባት የምስክር ወረቀት ለዜጎቿ አዘጋጅታለች።

ወደ ሲኒማና ቴአትር ቤቶች ወይም የገበያ ማዕከላት ለመግባት ይህንን ወረቀት ማሳየት ግዴታ ይሆናልም ተብሏል።

ኢኳዶር የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ከተከሰተ ጀምሮ 33 ሺህ 600 ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዘ ሞት መዝግባለች።