ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ ጉዳይ ላይ ዛሬ ይወያያል
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ዛሬ ሰኞ እንደሚወያዩ ተነገረ።
ምክር ቤቱ በሚያካሂደው ስብሰባ ላይ የሚነሳው የኢትዮጵያ ጉዳይ ትኩረት የሚያደርገው በሰብአዊ እርዳታ ጉዳይ ላይ ሲሆን ነገር ግን የዕለቱ ዋነኛ አጀንዳ እንዳልሆነ ተገልጿል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት ትግራይ ውስጥ ከተቀሰቀሰ በኋላ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከ10 ጊዜ በላይ መወያየቱ ይታወሳል።
ሰኞ ታኅሣሥ 11/2014 ዓ.ም ይካሄዳል የተባለው ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲካተት የጠየቁት ኢስቶኒያ፣ ፈረንሳይ፣ አየርላንድ፣ ኖርዌይ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ሲሆኑ አጀንዳው በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ እንደ ተጨማሪ ርዕስ የሚነሳ ነው።
እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ እርዳታ ጉዳይን በተመለከተ ለፀጥታው ምክር ቤት አባላት የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሏል።
በጦርነቱ ምክንያት በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ ያለውን የሰብአዊ እርዳታ ሁኔታ በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ባለፈው ሳምንት ባወጣው ሪፖርት ላይ 9.4 ሚሊዮን ሰዎች እርዳታን እንደሚፈልጉ አመልክቷል።
የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባውን በተመለከተ ባወጣው ማብራሪያ ላይ እንዳለው የምክር ቤቱ አባላት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን የእርዳታ አቅርቦት ተደራሽነትን በተመለከተ ከኃላፊው ዝርዝር ማብራሪያን የማግኘት ፍላጎት አላቸው።
በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውና በሳምንት ሁለት ጊዜ ወደ መቀለ ይደረግ የነበው የአየር በረራ አገልግሎት መልሶ መጀመሩንና ከሁለት ሳምንት በፊት ደግሞ በአራት ቡድን የተከፈሉ ምግብ የጫኑ 157 የጭነት ተሽከርካሪዎች ትግራይ መግባታቸውን ድርጅቱ አመልክቷል።
በስብሰባው ላይ ማርቲን ግሪፊትስ በእርዳታ አቅርቦት ላይ ስለገጠሙ ተግዳሮቶች ማብራሪያ የሚሰጡ ሲሆን፣ የምክር ቤቱ አባላትም በቅርቡ በእርዳታ ሠራተኞች ላይ ስለተፈጸሙ ጥቃቶችና የእርዳታ አቅርቦት ዘረፋን በተመለከተ እንዲሁም በሁሉም ወገኖች ስለሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ያላቸውን አቋም ይገልጻሉ ተብሏል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ኮምቦልቻ ውስጥ ለእርዳታ የተዘጋጁ የተለያዩ አቅርቦቶች በህወሓት ኃይሎችና በአንዳንድ ነዋሪዎች መዘረፋቸውን መናገራቸው ይታወሳል።
ይህ የዛሬው ስብሰባ የሚካሄደው ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ አካሂዶ፣ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተከሰቱ የመብት ጥሰቶችን የሚመረምር ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች አካል እንዲቋቋም በድምጽ ብልጫ ከወሰነ በኋላ ነው።
ኢትዮጵያ ይህ ውሳኔ ቀደም ሲል የተካሄደውን ምርመራ እና እየተወሰዱ ያሉ የማስተካከያ እርምጃዎችን የሚያደናቅፍ ነው በማለት የተቃወመችው ሲሆን፤ ፖለቲካዊ ዓላማን በመያዝ በአገሪቱ ላይ ጫና ለማሳደር ያለመ በመሆኑ ከመርማሪው አካል ጋር እንደማትተባበር አሳውቃለች።
በኢትዮጵያ ከሚካሄደው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ጋር በተደጋጋሚ አለመግባባት ተከስቷል። ሰባት የድርጅቱ ሠራተኞችም በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል በሚል ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ መደረጉ ይታወሳል።
አንድ ዓመት ያስቆጠረው ጦርነት ከትግራይ ክልል ባሻገር ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሲሆን፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ እንደሚፈልጉ የመንግሥታቱ ድርጅት በቅርቡ አስታውቋል።