በኬንያ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን የ'በቃ' ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ሰልፍ አካሄዱ

ታትሟል

በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን የዓለም አቀፍ 'በቃ' እንቅስቃሴ አካል የሆነውን የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ።

በኬንያ ናይሮቢ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት፣ የኤርትራ ማኅበረሰብ አባላት እና የኢትዮ-ኬንያ ወዳጅነት ማኅበር መሆናቸው ተገልጿል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገቡ ነው ያሉት ሰልፈኞቹ በመፈክሮቻቸው ይህ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ጠይቀዋል። በተለይ ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች አገር እንደመሆኗ ይህንን አስተሳሰብ አሁን የማትቀበል ናት ብለዋል።

በሰልፉ ከኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን በተጨማሪ የሱዳን እና የሶማሊያ ዜጎችም የየአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ የእንቅስቃሴው ደጋፊነታቸውን አሳይተዋል። በመርኃ ግብሩ የተሳተፉ አካላትም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮ-ኬንያ ወዳጅነት ማኅበርን ወክለው መልዕክት ያስተላለፉት ተወካይ "ከኬንያዊነቴ በፊት አፍሪካዊ ነኝ፣ አፍሪካዊነቴ ሲከበር ኬንያዊነቴ ክብር ያገኛል፣ ስለዚህም የኢትዮጵያ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳይ ስለሆነ ራሳችንን ለማስከበር ሁላችንም የ'በቃ'ን እንቅስቃሴ ተቀላቅለናል" ብለዋል።

የኤርትራና የሶማሊያ ተወካዮችም ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ጫና በአፍሪካ ላይ የሚደረግ ጫና እንደሆነ ጠቅሰው ይህንን አይነት የውጭ ጫናን በጋራ መከላከል እንደሚገባም ገልጸዋል።

በሰልፉ ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን "እኛ አገራችን የምንለው ሌላ አገር ስለሌለን ያለችንን አገር አስከብሮ መኖር የግድ ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገራት መሪዎች ሰሞኑን እየተቀነቀነ ያለው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አፍሪካ ድምጽ ሊኖራት ይገባል የሚለው ጉዳይም በሰልፉ ታዳሚዎች ከተስተጋቡት መልዕክቶች መካከል አንዱ ነው።

አሁን ኢትዮጵያ የገጠማት የምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነት ችግርን አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድምጽ አልባ ከመሆኗ ጋር ያያያዙት ሰልፈኞቹ፣ የአፍሪካን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ይህ ጥያቄ ሊመለስ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሰልፉ ታዳሚዎች በብዛት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማን ከመያዝ ባሻገር አለባበሳቸውን እና አጊያጌጣቸውንም በአገራቱ ሰንደቅ ዓላማ ገልጸዋል። የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እና የመከላከያ ሰራዊት ፎቶ ያለባቸው መፈክሮች በብዛት ታይተዋል።

በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም "ይህ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላይ የተጣለውን አላስፈላጊ ማዕቀብ ለማስቆም እና በተመረጠ የኢትዮጵያ ሕጋዊ መንግሥት ላይ የሚደረግን ጫና የመቃወም ኃላፊነት አለበት" ብለዋል።

ሌላኛው አምባሳደሩ ያነሱት ጉዳይ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን አተያይ በተመለከተ ነው። "ጋዜጠኝነት ክቡር ሙያ ነው" ያሉት አምባሳደር መለስ ዓለም "አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማሸበር፣ የኢትዮጵያን ክብር ለማኮሰስ እና መንግሥትን ለማጠልሸት ተጠቅመውበታል" ብለዋል። በመሆኑም የተሳሳቱ መረጃዎችን ባለማጋራት እና ባለማሰራጨት ጉዳቱን መቀነስ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በሚዲያዎች እንደምትገለጸው አለመሆኗን ለማሳየት የአንድ ሚሊዮን ጉዞ ወደ አገር ቤት ፕሮግራም ሁነኛ ማሳያ ይሆናል ያሉት አምባሳደሩ በናይሮቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በእዚህ ፕሮግራም ለመሳተፍ የኬንያን ቅርበት እንደትልቅ አማራጭ ወስደው እንዲሳተፉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አምባሳደሩ እንዳሉት ኬንያ ኢትዮጵያዊያን ኬንያን እንደአገራቸው ቆጥረው እንዲኖሩ ከማስቻሏ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የኢትዮጵያን መንግሥት አቋም በመደገፏ እናመሰግናለን ብለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ በአገሪቱ ላይ በምዕራባውያን አማካይነት የሚደረገውን ጫና ለመቃወም የተጀመረው የበቃ እንቅስቃሴ በተለያዩ አገራት ውስጥም ተቀባይነት አግኝቶ እየተካሄደ ይገኛል።