ፓኪስታን ውስጥ በአንድ ባንክ ላይ በደረሰ የጋዝ ፍንዳታ 14 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በፓኪስታን ደቡባዊ ክፍል በትምገኘው የካራቺ ከተማ ውስጥ በአንድ ባንክ ላይ ባጋጠመ ፍንዳታ ቢያንስ 14 ሰዎች መሞታቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
ከጋዝ ማስተላላፊያ ቱቦ አፈትልኮ በወጣ ጋዝ ምክንያት የተፈጠረ ፍንዳታ እንደሆነ በተገመተው በዚህ አደጋ ከሟቾቹ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የዓይን እማኞች ለፓኪስታን መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት በርካታ ሰዎች በፍርስራሾች ውስጥ ይገኛሉ። በዚህም ምክንያት በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል ስጋት አለ።
ፍንዳታው ከደረሰበት ስፍራ የወጡ ምስሎች እንደሚያሳዩት ባንኩ ያለበት ህንጻ መስኮቶችና በሮች ተገነጣጥለው የወደቁ ሲሆን፣ የባንኩ ሰነዶች በአካባቢው ባለ መንገድ ላይ ተበታትነው ይታያሉ እንዲሁም ከህንጻው ውጪ የነበሩ ተሽከርካሪዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
"ፍንዳታው በምን ምክንያት እንደደረሰ ለማወቅ የፍንዳታ ባለሙያዎቻችን ቡድን ምርመራ እያደረገ ነው። ነገር ግን ህንጻው የተገነባበት አካባቢ ባለው የፍሳሽ መስመር በተከሰተ የጋዝ ፍንዳታ ሊሆን ይችላል" ሰሉ የአካባቢው ፖሊስ ባለሥልጣን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
አደጋው የደረሰበት ሐቢብ የተባለው ባንክ በትዊተር ላይ ባስተላለፈው መግለጫ "ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በባንካችን አንድ ቅርንጫፍ ላይ የፍንዳታ አደጋ አጋጥሟል" ሲል የደረሰውን አረጋግጧል።
ጨምሮም በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች ቤተሰቦችም የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ባንኩ ባወጣው መግለጫ ላይ ገልጿል።








