ራፐር ድሬኮ ዘ ሩለር በሎስ አንጀለስ የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ በስለት ተወግቶ ሕይወቱ አለፈ

ታትሟል

በመድረክ ስሙ ድሬኮ ዘ ሩለር በሚል የሚታወቀው እውቁ አሜሪካዊው ራፐር ዳሬል ካልድዌል በሎስ አንጀለስ በተካሄደ የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ በስለት ተወግቶ ሕይወቱ አለፈ።

የ28 ዓመቱ ወጣቱ ሙዚቀኛ ቅዳሜ ምሽት 'ዋንስ አፕኦን ኤ ታይም' በተባለው የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ ሥራዎቹን ለማቅረብ ፕሮግራም ይዞ ነበር።

ይሁን እንጂ የእርሱ የማስታወቂያ ባለሙያ እሁድ ጠዋት ድሬኮ ዘ ሩለር ይህችን ዓለም መሰናበቱን ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን አሳውቋል።

አርቲስቱ የሙዚቃ ዝግጅቱን ሊያቀርብ በነበረበት ወቅት ከመድረኩ ጀርባ በተፈጠረ አለመግባባት በስለት መወጋቱ ተነግሯል።

የሎስ አንጀለስ ፖሊስ ጉዳዩን እየመረመረ እንደሆነ፤ ነገር ግን እስከ እሁድ ጠዋት ድረስ ከግድያው ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው አለመኖሩን ለጋዜጠኞች ገልጿል።

ድሬኮ ዘ ሩለር በስፖቲፋይ ላይ ከ1.5 ሚሊየን በላይ ወርሃዊ አድማጮች ነበሩት።

ከካናዳዊው ራፐር ድሬክ ጋርም 'ቶክ ቱ ሚ' የተሰኘ ነጠላ ዜማ አበርክቷል።

ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የድንገተኛ አደጋ የሕክምና ባለሙያዎች ቅዳሜ ምሽት 2፡30 ለደረሳቸው የአደጋ ጥሪ በቦታው ደርሰው ምላሽ ሰጥተዋል።

ከዚያ በኋላ ግን ወጣቱ ራፐር ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ከቆይታ በኋላ በደረሰበት ጉዳት ሳቢያ ሕይወቱ ሊያልፍ መቻሉ ተዘግቧል።

ቢቢሲ አስተያየት እንዲሰጡ የራፐሩን ወኪሎች ጠይቆ ነበር።

የሙዚቃ ፌስቲቫሉ አሰናጅ የሆነው 'ላይቭ ኔሽን' ከመድረኩ በስተጀርባ አለመግባባት እንደነበር አረጋግጧል።

በሙዚቃ ዝግጅቱ ላይ የራፐር ፊፍቲ ሴንት እና የስኑፕ ዶግ የሙዚቃ ሥራዎችንም ለማካተት ታቅዶ ነበር።

"ታዳሚዎችን በማክበር እና ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር በመተባበር አርቲስቶችና አዘጋጆች መርሃ ግብሩን ላለማካሄድ ወስነው ፌስቲቫሉ ማብቃት ከነበረበት አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ ተጠናቅቋል" ብሏል።

የራፐር ድራኮን ሞት ተከትሎ በርካቶች ሐዘናቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየገለፁ ይገኛሉ።

የሎስ አንጀለስ ጸሐፊ ጄፍ ዌስ በትዊተር ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ "አዲስ የራፕ ቋንቋ የፈጠረ፣ ነርቭ የሚነኩ ዜማዎች እና ቃላቶች የፈለሰፈ የትውልዱን ታላቅ አርቲስት ነበር" ሲል ገልጾታል።