በጃፓን አንድ ሕንጻ ላይ በተቀሰቀሰ እሳት ቢያንስ 27 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተገለጸ

በእሳት አደጋው የተለበለቡ መስኮቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በጃፓን ኦሳካ ከተማ በሚገኝ አንድ ሕንጻ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ቢያንስ 27 ሰዎች ለህልፈት ሳይዳረጉ እንዳልቀረ ተገለጸ።

ፖሊስ እሳቱ ሆን ተብሎ የተነሳ መሆን አለመሆኑን እያጣራ ነው ሲል አንድ በአገሪቱ የሚገኝ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የተጎጂዎቹ ሞት በይፋ ከመገለጹ አስቀድሞ ባወጧቸው ዘገባዎች ሟቾች በአደጋው "የልብ ሥራ መስተጓጎል" እንደገጠማቸው ሲያመላክቱ ነበር።

በርካታ የእሳት አደጋ ተከላካይ ሰራተኞች በሕንጻው አራተኛው ፎቅ የተነሳውን እሳት ካጠፉት በኋላ በጭስ የጠቆሩ መስኮቶችም ታይተዋል።

የነፍስ አድን ሰራተኞች አርብ ማለዳ ላይ የእሳት አደጋው በተከሰተ በ30 ደቂቃ ደርሰው በ20 ካሬ ሜትር የተነሳውን ቃጠሎ በተሳካ ሁኔታ መቆጣጠር መቻሉን የአካባቢው የእሳት አደጋ መከላከያ መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

ለሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት የሆነው እሳት የተነሳበት ሕንፃ በኦሳካ ውስጥ በሚገኝ የንግድ እና መዝናኛ አካባቢ ውስጥ የሚገኝ ነው።

ባለፈው ዓመት አንድ ግለሰብ በቶክዮ የሚገኝ የፊልም ስቱዲዮ ላይ እሳት በማስነሳቱ የ36 ሰዎች ሕይወት አልፏል።

አደጋው በጃፓን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በጅምላ ከተከሰቱ አሰቃቂ አደጋዎች መካከል አንዱ ነው ተብሏል።