ዝናው በዓለም የናኘው የናይጄሪያ አደገኛ የወንጀለኞች ቡድን በቢቢሲ ተጋለጠ

መናኸሪያውን ናይጄሪያ ያደረገ አንድ የአደገኛ ወንጀለኞች ቡድን ከግድያና ሙስና አልፎ የአገሪቱን ፖለቲካ እየዘወረ ዓለም አቀፍ የአታላዮች መረብ መዘርጋቱን ቢቢሲ እጅ የገባ ሰነድ ጠቆመ።
ቢቢሲ ያገኛቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ መዛግብትና ምስክሮች እንደሚጠቁሙት ቡድኑ ከናይጄሪያ ድንበር አልፎ በተለያዩ አገራት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
'ብላክ አክስ' የተሰኘው የወንጀለኞች ቡድን ናይጄሪያ ውስጥ ለዓመታት ሲንቀሳቀስ የቆየና አሉ ከሚባሉ አደገኛ ቡድኖች መካከል አንዱ እንደሆነ ተደርሶበታል።
ናይጄሪያ ውስጥ የመሰል ቡድኖች አባል መሆን በሕግ የተከለከለ ነው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የቢቢሲ መርማሪ ጋዜጠኞች ቡድን ቢቢሲ አፍሪካ አይ ይህን ብላክ አክስ የተሰኘ ቡድን ሲከታተል፤ የቀድሞ አባላትን ሲያናግር እንዲሁም በርካታ ሰነዶችን ሲሰበስብ ቆይቷል።
ምንም እንኳ የሁሉንም ሰነዶች ምንጭ ማጣራት ባይቻልም ከመካከላቸው ቁልፍ የሚባሉ የቡድኑን ማንነት ግልጥ አድርገው የሚያሳዩ ሆነው ተገኝተዋል።
ቢቢሲ መርምሮ ከደረሰባቸው ማስረጃዎች መካከል አንዱ የኢሜይል መልዕክት፣ ዝነኛው ናይጄሪያዊ የንግድ ሰውና በፈረንጆቹ 2019 የኤፒሲ ፓርቲ ዕጩ የነበረው ኦገስተስ ቤሚጎ የብላክ አክስ የቀድሞ አባል እንደሆነና በርካታ ሚሊዮን ዶላር ያፈሰበትን የማታለል ድርጊት መፈጸሙን ጠቁሟል።
ከቤሚጎ ኢሜይል ጋር ግንኙነት ያላቸው 18 ሺህ ገደማ ገፅ የሚሆኑ ፋይሎች ግለሰቡ ለአጋሮቹ 62 ጊዜ የማታለል ተግባርን የሚያሳይ መመሪያ መላኩን እንዲሁም የማታለል ተግባሩ ዒላማ ለሆኑ ሰዎች መልዕክት መስደዱን ያሳያሉ።
"አንድ ሚሊዮን ዶላር አካባቢ አግኝተንበታል" ይላል አንድ ለቤሚጎ የተላከ ኢሜይል። ይህ መልዕክት የማታለል ተግባሩ ሰለባን ስምና አድራሻ እንዲሁም የስልክ ቁጥር አልፎም የማታለያ መመሪያን ያዘለ ነው።
ቢቢሲ ሌሎች ሁሉት የቤሚጎ ኢሜይል ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ተከታትሎ ደርሶባቸው በድምሩ 3.3 ሚሊዮን ዶላር እንደተጨበረበሩ ይናገራሉ።
በዓለም አቀፍ የሕግ አስፈፃሚ አካላት የተሠሩ ምርመራዎች እንደሚጠቁሙት ብላክ አክስ የተሰኘው ይህ ቡድን እስካሁን ያጭበረበረው ገንዘብ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሊሆን ይችላል።
ቢቢሲ የቤሚጎን አስተያየት ለመቀበል ጥረት ቢያደርግም ግለሰቡ ስለቀረበበት ወቀሳ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።
አንዳንድ ሾልከው የወጡ ወረቀቶች ያዘሉት አሰቃቂ ምስል ለሕትመት ብቁ ባለመሆናቸው ይፋ አልሆኑም። ነገር ግን ቡድኑ ከ2009 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ከዋና መናኸሪያው ኤዶ ግዛት ሆኖ የናይጄሪያ ፖለቲካን ዘልቆ መግባቱን እኒህ ፋይሎች ይጠቁማሉ።
ሁሉት ዶክመንቶች በቤኒን ከተማ 35 ሚሊዮን ናይራ ወደ ዶላር ሲመነዘር 62 ሺህ የሚሆን ገንዘብ ኔዮ-ብላክ ሙቭመንት ኦፍ አፍሪካ ወደተሰኘው ቡድን የባንክ ደብተር እንደተላከ ያሳያሉ።
ይህ ቡድን ናይጄሪያ ውስጥ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ሲሆን በምዕራባዊያን ሕግ አስከባሪ ድርጅቶች በዓይነ ቁራኛ የሚታይና ልክ እንደ ብላክ አክስ አደገኛ ተደርጎ የሚታይ እንዲሁም በ2012 የናይጄሪያ ምርጫ እጁ አለበት የሚባል ነው።
መዛግብቱ እንደሚጠቁሙት ይህ ባንክ በወቅቱ ላደረገው ድጋፍ "በክልል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለኤንቢኤም ቤኒን ዞን ሰዎች የተተው 80 ክፍት የሥራ ቦታዎች" ተሰጥቶታል።
በቤኒን ከተማ ወጣቶች ብላክ አክስን የመሳሰሉ የወንጀለኛ ቡድኖችን እንዳይቀላቀሉ የማንቃት ሥራ በመሥራት የሚታወቀው ከርቲስ ኦጌጌቦር "የናይጄሪያ ፖለቲካ የማፍያ መጫወቻ ሆኗል" ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።
"የግለሰብ አምልኮ ከላይ እስከ ታች ባለው የመንግሥት እርከን ላይ የሚስተዋል ነገር እየሆነ መጥቷል፤ ሀሉም ቦታ ልታገኟቸው ትችላላችሁ" ይላሉ ከርቲስ።
ኔዮ-ብላክ ሙቭመንት ኦፍ አፍሪካ ከብላክ አክስ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለኝም ሲል የቀረበበትን ክስ በፅኑ ተቃውሟል። አልፎም የቡድኑ ጠበቃ ማንኛውም ከብላክ አክስ ጋር ግንኙነት ያለው አባል "ወዲያውኑ ይባረራል" ብለዋል።
ኤንቢኤም የተሰኘው ቡድኑ በመላው ዓለም ከሦስት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉኝ የሚል ሲሆን፤ ለወላጅ አልባ ሕፃናት፣ ለትምህርት ቤቶች እንዲሁም ለናይጄሪያና ለሌሎች አገራት ፖሊሶች እርዳታ ሲያደርግ የሚያሳዩ ምስሎችን ያትማል።
"ኤንቢኤም ብላክ አክስ አይደለም። ኤንቢኤም ከወንጀል ጋር ምንም ግንኙነት የለውም" ሲሉ የቡድን ፕሬዝደንት ኤሴ ካኮር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነገር ግን ዓለም አቀፍ ሕግ አስከባሪ ድርጅቶች ስለኤንቢኤም ያላቸው አመለካከት ለየት ያለ ነው። የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር ኤንቢኤምን "ወንጀለኛ ድርጅት" ሲል የሰየመው ሲሆን "የብላክ አክስ ከንፍ" ነው ይላል። የካናዳ ባለሥልጣናትም ብላክ አክስና ኤንቢኤም "ተመሳሳይ ናቸው" ብለዋል።
የአሜሪካ ደኅንነት መሥሪያ ቤት፣ ኤፍቢአይ እና ኢንተርፖል በቅርቡ ብላክ አክስን ዒላማ አድርገው ምርመራ ካደረጉ በኋላ 35 የኤንቢኤም አባላትን አሜሪካና ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በቁጥጥር ሥር አውለዋል።
ግለሰቦቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በበይነ መረብ እርዳታ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች አጭበርብረዋል በሚል ነው። ኤንቢኤም እነዚህ አባላቱ ከድርጅቱ ለጊዜ መታገዳቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።
በ2017 ከብላክ አክስ ጋር ግንኙነት ያለው የገንዘብ ማጭበርበሪያ መንገድን መበጣጠሳቸውን የካናዳ ባለሥልጣናት ይፋ አድርገው ነበር። ይህ ገንዘብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሆነ በወቅቱ የካናዳ ባለሥልጣናት ገልጠው ነበር።
በአሁኑ ወቅት ምን ያህል የገንዘብ ማጭበርበሪያ መንገዶች ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሆነ በውል ባይታወቅም መዛግብቱ፤ አባላቱ ሌጎስ፣ ለንደን፣ ዱባይ እንዲሁም ሌሎች በርካታ አገራት ውስጥ ሆነው ግንኙነት እንደሚያደርጉ ያሳያሉ።
ናይጄሪያ ውስጥ ብላክ አክስ የተሰኘው ቡድን የሚታወቀው በየጎዳናው በሚፈፅመው ወንጀልና አሰቃቂ ድርጊት እንዲሁም ከፖለቲከኞች ጋር ባለው ግንኙነት ነው።
ነገር ግን ይህ ቡድን ከፖለቲከኞች ጋር ያለው ግንኙነት በግልፅ የሚታወቅ አይደለም።
ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም አቀፍ የመገናኛ አውታር የተናገሩት የኤዶ ግዛት አስተዳደር የቀድሞ አባል የሆኑ አንድ ግለሰብ የብላክ አክስ አባልነት በናይጄሪያ ፖለቲካ ውስጥ እጅግ ሰርጎ የገባ ነው ይላሉ።
"ቁጭ አድርጋችሁ እዚህ የብላክ አክስ አባላት የሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጥራ ብትሉኝ እዘረዝርላችኋለሁ" ይላሉ ቶኒ ካባካ።
ግለሰቡ ከሥልጣናቸው ከወረዱ በኋላ በተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ እንደተረገባቸውና አሁን የሚኖሩበት መኖሪያ ቤት የግቢ በር በጥይት እንደተበሳሳ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
"አብዛኞቹ ፖለቲከኞች፤ ከሞላ ጎደል ሁሉም እጃቸው አለበት" ይላሉ።
ቢቢሲ ለኤዶ ግዛት ባለሥልጣናት ከብላክ አክስ ጋር ግንኙነት አላችሁ ወይ የሚል ጥያቄ ቢልክም እስካሁን ምላሽ አላገኘም።












