ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጆ ባይደን የአገሪቱን ከፍተኛ የክብር ኒሻን ለመጀመሪያ ጊዜ ለጥቁር አሜሪካዊ ወታደር ሸለሙ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአገሪቱን ከፍተኛ የወታደራዊ ኒሻን ሽልማት ለሦስት አሜሪካዊያን ሸልመዋል።
ከእነዚህ ተሸላሚዎች ውስጥ አንዱ አሁን በሕይወት የሌለ ጥቁር አሜሪካዊ ወታደር ሆኗል።
አንድ ጥቁር አሜሪካዊ ለዚህ የአገሪቱን ከፍተኛ ወታደራዊ ኒሻን ሽልማት ሲበቃ ከቬትናም ጦርነት ወዲህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
ይህ ጥቁር ወታደር ሳጅን አልዊን ካሼ ይባላል።
በኢራቅ ጥይት የማይበሳው የወታደር ተሸከርካሪ ላይ የነበሩ ባልደቦቹ ተሸከርካሪያቸው በተጠመደ ቦምብ ምክንያት በእሳት እየነደደ እንደሆነ በመመልከቱ እነሱን ለማዳን ሲል ዘሎ ራሱን አደጋ ላይ ጭምር በመጣል ለፈጸመው ጀብዱ ነው ይህ ሽልማት የተበረከተለት።
ወታደር ካሼ በወቅቱ የ6 ባልደቦቹን ሕይወት ቢታደግም በወቅቱ በደረሰበት የእሳት አደጋ የተነሳ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት፣ ከሦስት ሳምንት በኋላ ሕይወቱን ያጣ ሲሆን በጊዜው የፈጸመው ጀብዱ ግን በታሪክ የሚዘከር ሆኖለታል።
ጆ ባይደን ናቸው ለዚህ ወታደር ነው ትልቁን የአሜሪካ ብሔራዊ የክብር ኒሻን መታሰቢያ ያበረከቱት፡፡
ይህ ጥቁር ወታደር አሜሪካ ኢራቅና አፍጋኒስታን ከገባች ወዲህ የክብር ኒሻን በስሙ የተበረከተለት የመጀመርያው ጥቁር ሆኗል።
ሳጅን ካሼ በጊዜው ዕድሜው 35 ነበር።
ጆ ባይደን ይህን ጥቁር አሜሪካዊ "የወታደሮች ሁሉ ወታደር፣ የጀግኖች ሁሉ ጀግና፣ ጓደኞቹን ለማትረፍ በእሳት ላይ የተራመደ ብርቱ" ሲሉ አሞካሽተውታል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ይህን ታላቅ ጀብዱ የፈጸመው ጥቁር አሜሪካዊው ሚስት እና ልጆች ተገኝተዋል።
ምንም እንኳ ይህን ሽልማት ለማግኘት የሚታጩ የአሜሪካ ወታደሮች ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ብቻ የተፈጸሙ ጀብዱዎች እንደ መመዘኛ የሚታዩ ቢሆንም፣ ለሳጅን ካሼ ጀግንነት ግን ኮንግረሱ ተሰብስቦ በልዩ ሁኔታ ዕጩ ሆኖ እንዲቀርብ ወስኖለታል።
በዚህ የተነሳም ነው ጀብዱው ከተፈጸመ ረዘም ያለ ጊዜ ቢያስቆጥርም ኒሻኑ እንዲበረከት የተደረገው።
ዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ እንደዘገበው ይህ ሽልማት ባለፈው ዓመት ዶናልድ ትራምፕ ሊሰጡት ያሰቡት ሽልማት የነበረ ቢሆንም ነውጠኛ ደጋፊዎቻቸው በካፒቶል ሂል ባስነሱት ረብሻ ምክንያት ሁኔታዎች ሌላ መልክ በመያዛቸው ለዘንድሮ የተላለፈ ነው።