የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በጦር ኃይሉ ተሹመው የነበሩ አስተዳዳሪዎችን አሰናበቱ

አብደላ ሐምዶክ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ
ታትሟል

የሱዳን ጦር መፈንቅለ መንግሥት አካሂዶ ሹመት ሰጥቷቸው የነበሩ የክልል አስተዳዳሪዎችና ሚኒስትሮች በጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክ ከኃላፊነታቸው ተሰናበቱ።

ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ በቁም እስር ላይ የነበሩት እና ዳግም ወደ ሥልጣን የተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ከክልል አስተዳዳሪዎች በተጨማሪ በጦሩ ተሹመው የነበሩ ሚኒስትሮችንም አንስተዋል።

አብደላ ሐምዶክ ከሥልጣን ያነሷቸው ሚኒስትሮች ከቀድሞው የሱዳን የረዥም ጊዜ መሪ ኦማር አል በሽር መንግሥት ጋር ቁርኝት የነበራቸው ናቸው ተብሏል።

ከጥቂት ወራት በፊት የሱዳን ጦር በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ የሚመራውን የሲቪል መንግሥት ገልብጦ ሥልጣን ተቆጣጥሮ እንደነበረ ይታወሳል።

አብደላ ሐምዶክ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ወደ ሥልጣናቸው የተመለሱት በጄነራል አብድል ፈታ አል ቡርሐን ከሚመራው መፈንቅለ መንግሥት አድራጊ ኃይል ጋር ባደረጉት ስምምነት ነው።

ጄነራል አል-ቡርሐን ወደ ሥልጣናቸው እንዲመለሱ ከተደረጉት የሲቪል መንግሥቱ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር አብሮ ለመሥራት እና ምርጫ እስኪከናወን ድረስ አብደላ ሐምዶክ ለሚመሰርቱት የሽግግር መንግሥት ድጋፍ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

ሱዳናውያን ግን የወታደራዊ ሥርዓቱ አሁንም በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ያለው ሚና መቀጠሉ እንዳስቆጣቸው በመግለጽ ተጨማሪ የአደባባይ ላይ ተቃውሞዎች ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ድምጻቸውን በአደባባይ ለማሰማት የሚወጡ ሰዎች በሱዳን ጦር መሪዎች ላይ ያላቸው ተቃውሞ እና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ያላቸውን ድጋፍ ሲገልጹ ቆይተዋል።

በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ሠራዊቱ መፈንቅለ መንግሥት አካሂዶ የሲቪል አስተዳደሩን አመራሮች ከበተነና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከደነገገ በኋላ መፈንቅለ መንግሥቱን ተቃውመው አደባባይ ከወጡ መካከል ቢያንስ 40 የሚሆኑ ሰዎች ተገድለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ምዕራባውያን አገራት እና የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ በርካቶች መፈንቅለ መንግሥቱን በመቃወም፤ የአገሪቱ ዜጎች ሱዳን ወደ ሰላማዊ የዲሞክራሲ ሽግግር እንድትመለስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ሲጠይቁ ነበር።