ጋና የኮሮናቫይረስ መከላከያ ያልተከተቡ መንገደኞች ወደግዛቷ እንዳይገቡ ከለከለች

ታትሟል

ጋና በመላው ዓለም ካሉ ጥብቅ የኮቪድ-19 የጉዞ ሕጎች አንዱ በተባለው መርህ ክትባት ያልወሰዱ መንገደኞች ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ከለከለች።

በተጨማሪም የአገሪቱ ዜጎች ወይም ነዋሪዎች በአውሮፕላን ማረፊያው ሲደርሱ ክትባት እንዲወስዱ የሚያስገድድ ሕግ ተግባራዊ አድርጋለች።

ሕጉ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን ክትባት ሳይወስዱ ራስን አግልሎ የማቆየት አማራጭ እንደሌለ ተነግሯል።

የአገሪቱ ባለሥልጣኖች በዚህ የዓመት በዓል ወቅት የኮቪድ-19 ስርጭት መጠን ያሻቅባል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የጋና የምድር እና የባሕር በሮች ኮሮናቫይረስ ከጀመረበት ግዜ ጀምሮ ለመንገደኞች ዝግ ሆነው ቆይተዋል።

ከክትባቱ ባሻገር ተጓዦች የኮቪድ-19 ምርመራ ወረቀታቸውን ይዘው መገኘት እና ከጋና የሚወጡ ሁሉም ጋናዊያን ተጓዦች በሙሉ ክትባቱን መውሰድ ይገባቸዋል።

ይህም ማለት አንድ ተጓዥ የጆንሰን እና ጆንሰን ክትባትን የሚወስድ ካልሆነ በስተቀር ከአገር ከመውጣቱ በፊት ሁለተኛውን ክትባት እስከሚወስድ መጠበቅ ይገባዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ለአስትራዜኒካ ክትባት በመጀመሪያው ክትባት እና በሁለተኛው መሃል ከስምንት እስከ 12 ሳምንት ክፍተት እንዲኖር ይመክራል። ለፋይዘር ደግሞ ከ21 እስከ 28 ቀናት ልዩነት ሊኖር ይገባል። የሞደርና እና የስፑትኒክ ቪ ክትባቶችም በተመሳሳይ የሁለት ዙር ክትባትን ይፈልጋሉ።

የጋና ባለሥልጣናት ከአዲሱ የኦሚክሮን ዝርያ ጋር በተያያዘ ከውጪ አገር በሚመጡ መንገደኞች አማካኝነት አዲስ የኮቪድ-19 የስርጭት ማዕበል እንዳይኖር ስጋት ገብቷቸዋል።

«በዚህ የዓመት በዓል ወቅት ሊኖር የሚችለው የቫይረሱ የስርጭት መጠን ስጋት አስቸኳይ እርምጃዎችን እንድንወስድ አስገድዶናል» ሲሉ ፓትሪክ ኪማ አቦጋዬ የተሰኙት የአገሪቱ የጤና አገልግሎት ኃላፊ ተናግረዋል።

ኃላፊው አክለውም ባለፈው ሁለት ሳምንታት በጋና አውሮፕላን ማረፊያ የተገኙ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር በአገሪቱ ካለው አዲስ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ውስጥ 60 በመቶውን ይሸፍናል ብለዋል።

አዲሱን የኮቪድ-19 ክልከላዎች ከፊሉ ጋናዊያን ትክክለኛ እርምጃ ነው ቢሉትም ሌሎች ደግሞ ሰዎች የመምረጥ መብት ሊኖራቸው ይገባል የሚል አቋም መያዛቸውን የቢቢሲው ፌቨር ኑኖ ከጋና ዘግቧል።

በአገሪቱ ካለው ዝቅተኛ የቫይረሱ ስርጭት ጋር ተያይዞም በርካታ ጋናዊያን በወረርሽኙ ምክንያት ስጋት እንዳልገባቸው እና ክትባቱንም የመውሰድ ፍላጎት እንደማያሳዩ አክሎ ገልጿል።

እስካሁንም 10 በመቶው የጋና ሕዝብ ብቻ ክትባቱን የወሰደ ሲሆን ይህም በተለይም ከክትባት እጥረት ጋር የተያያዘ ነው።

«ወደ ጋና ለመምጣት ካሰባችሁ ክትባት ለመውሰድ ፈቃደኛ ናችሁ ማለት ነው» ሲሉ የጤና ሃላፊው ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል።

በጋና በመጨረሻው የኮቪድ ማእበል ወቅት ወደ ሆስፒታል ከገቡ የኮቪድ ሕሙማን ውስጥ 90 በመቶው ክትባት ያልወሰዱ ናቸው ሲሉም አክለዋል።

በመጪው ወር መንግስት ሕብረተሰቡ ክትባት እንዲወስድ እቅድ ይዟል። ይህም የመንግስት ሰራተኞች፥ ተማሪዎች እና የጤና ሰራተኞች ክትባቱን እንዲወስዱ ግዴታ የማስቀመጥ እቅድን እንደሚያጠቃልል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

እንደ የምሽት ክበብ ብሎም ስታዲየም የመሳሰሉ በርካታ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸው አካባቢዎች ለመግባት የክትባት ፓስፖርትን መያዝ ግዴታ እንደሚሆንም ተቀምጧል።

የኮቪድ ወረርሺኝ ከተከሰተ ጀምሮ ጋና ከ130 ሺህ በላይ የኮቪድ ሕሙማንን ብሎም 1228 ሞት መዝግባለች።