ፌደራል ፖሊስ ዓለም አቀፍ አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ

ኮኬይን

የፎቶው ባለመብት, federal police Facebook

ታትሟል

ከብራዚሏ ከተማ ሳኦፖሎ የተነሱና መዳረሻቸው ዱባይና ናይጄሪያ ያደረጉ ሶስት የአደገኛ አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

ዕፅ አዘዋዋሪዎቹ ሁለት ናይጄሪያዊያንና አንዲት ብራዚላዊት መሆናቸውንም ፌደራል ፖሊስ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ በቦሌ አየር ማረፊያ በተደረገባቸው ፍተሻ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል ብሏል።

ግለሰቦቹ አደንዛዥ ዕፁን በውስጣዊ የሻንጣ አካል እንዲሁም በሆዳቸው ውጠው ለማለፍ ቢሞክሩም በተደረገባቸው ጥብቅ ፍተሻ ሊገኙ መቻላቸውን አክሎ ገልጿል።

ፖሊስ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ሶስት የዕፅ አዘዋዋሪዎች መካከል ብራዚላዊቷ ከ13 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን 666 ጥቅል በፍሬና እንዲሁም ከ17 ኪሎግራም በላይ የሚመዝን በዱቄት መልክ 11 እሽግ ኮኬይን በሻንጣዋ ውስጥ ይዛ ተገኝቷል።

ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱ ናይጄሪያውያን አደንዛዥ ዕፁን በሆዳቸው ይዘው ሊያዘዋውሩ እንደሚችሉ በመጠርጠሩ በፌደራል ፖሊስ ሆስፒታል ምርመራ የኤክስሬይ ምርመራ ተደርጎላቸዋል ብሏል።

በምርመራውም 1 ሺህ 650 ግራም የሚመዝን 83 ፍሬ ኮኬይን ከሆዳቸው እንዲወጣ መደረጉ ተገልጿል፡፡

ሰዎችን ለወንጀል የሚያነሳሳ በመሆኑ እንዳይዘዋወር፣ እንዳይመረት እና በጥቅም ላይ እንዳይውል በህግ የተከለከለ አደገኛ ዕፅ ይዘው ሲያዘዋዉሩ የተገኙት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑንም መግለጫው አክሏል።