ጣልያናዊው የኮሮናቫይረስ ክትባት ላለመወጋት ሰው ሠራሽ ክንድ ገጥሞ ሆስፒታል ሄደ

ታትሟል

አንድ ጣልያናዊ የኮሮናቫይረስ ክትባት ላለመወጋት ብሎ ሰው ሠራሽ ክንድ ገጥሞ ወደ ሆስፒታል ሄዷል።

ክንድ የሚመስል ከፕላስቲክ የተሠራ ሰው ሠራሽ ክንድ የገጠመው ጣልያናዊ 50 ዓመቱ ነው። የኮሮናቫይረስ ክትባት ሰርተፍኬት ቢፈልግም ክትባቱን ግን መውሰድ አልፈለገም።

እናም ክንዱ ላይ ሰው ሠራሽ የፕላስቲክ ክንድ ሰክቶ ወደ ሆስፒታል ለመሄድ ወሰነ።

እንደጠበቀው ግን ሐኪሞቹን ማታለል አልቻለም።

ክትባት የምትሰጠው ነርስ ክንዱን ስትይዘው "የሚዋዥቅ፣ ቀዝቃዛ እና በጣም ቀላል" ሆኖ እንዳገኘችው ተናግራለች።

ሰው ሠራሽ ክንድ እንደሆነ ስትደርስበት፤ ግለሰቡ 'እንዳላየሽ እለፊው' ብሏትም ነበር። ነርሷ ግን ለፖሊስ ጠቁማለች።

በጣልያኗ ቢይላ ግዛት የተከሰተውን ፖሊስ እየመረመረ ይገኛል። ባለሥልጣናትም ግለሰቡን እየወቀሱት ነው።

የአካባቢው አስተዳዳሪ አልበርት ቺሪዩ "እንዲህ አይነት ዋልጌነት ያሳፍራል። አገራችን በወረርሽኙ ሳቢያ ማኅበራዊና የምጣኔ ሀብት ዋጋ መክፈሏን ያላገናዘበ ነው" ብለዋል።

ጉዳዩን የበለጠ መነጋገሪያ ያደረገው ግለሰቡ የጤና ባለሙያ መሆኑ ነው። በተጨማሪም ክትባት አልወስድም በማለቱ ነበር ከሥራ የተሰናበተው።

ጣልያን ሁሉም የጤና ባለሙያዎቿ እንዲከተቡ መመርያ ሰጥታለች።

'ላ ሪፐብሊካ' እንደዘገበው፤ ግለሰቡ ሰው ሠራሽ ክንድ አድርጎ ሆስፒታል መሄዱ ሳያንሰው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሌሎች ሰዎችም የእሱን ፈለግ እንዲከተሉ የሚያነሳሳ ጽሑፍ ለጥፏል።

ሰው ሠራሽ ክንድ እና አንገት ያለው የሰውነት መሸፈኛ አማዞን ላይ በ416 ዶላር ይሸጣል።

ይህንን የሰውነት መሸፈኛ ፎቶ የለጠፈ አንድ የትዊተር ተጠቃሚ "ይሄንን የሰውነት መሸፈኛ አድርጌ ብሄድ ሆስፒታሉ ያውቅብኝ ይሆን? መርፌው ሰውነቴን እንዳይነካው ልብስ ደራርቤ መልበሴም አይቀርም" ሲል ጽፏል።

ጣልያናውያን ከነሐሴ ወዲህ ወደ መዝናኛ፣ ስፖርት ማዘውተሪያ ወይም ሲኒማ ቤት ለመሄድ የክትባት ሰርተፍኬት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።

አሁን ደግሞ ሕጉ ተሻሽሎ፤ በአገሪቱ አገልግሎት መስጫዎች መገኘት የሚችሉት በቅርቡ የተከተቡ ወይም በቅርቡ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ሆነዋል።

ሕጉ በብዙ የጣልያን ከተሞች ተቃውሞ ገጥሞታል።

ከ73 በመቶ በላይ የአገሪቱ ዜጎች ሙሉ በሙሉ ተከትበዋል። ቁጥሩ ከፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም ይበልጣል። ከስፔን እና ፖርቹጋል አንጻር ግን ያንሳል።