ደቡብ አፍሪካ 'ተዘረፍኩ' ያለችውን የጋና ግጥሚያ እንዲደገም ልትጠይቅ ነው

የደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን (ሳፋ) እሑድ ምሽት ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ጋና አቅንቶ ባደረገው ወሳኝ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ላይ ዳኞች ባሳዩት ብቃት ዙሪያ አቤቱታውን ለፊፋ ሊያስገባ ነው።
ደቡብ አፍሪካ ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻውን ዙር ለማለፍ ከጋና ጋር አቻ መለያየት ብቻ ያስፈልጋት ነበር። ይሁን እንጂ ጋና አወዛጋቢ በሆነ ፍጹምቅጣት ምት 1 ለ 0 አሸንፋለች።
ጋና በጠባብ ውጤት በማሸነፍ ለአፍሪካ የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ውድድር ለመድረስ ችላለች። ጋና ከደቡብ አፍሪካ በላይ ለመሆንም በግብ ልዩነት በልጣ ነው ምድቡን በቀዳሚነት ማጠናቀቅ የቻለችው።
የፍጹም ቅጣት ምቱ የተሰጠው ጋናዊው የሌስተር ሲቲ አማካይ ዳንኤል አማርቴይ በደቡብ አፍሪካው ተከላካይ ሩሺን ዴ ሬውክ ትንሽ በሚመስል ንክኪ መውደቁን ተከትሎ ነው። ተከላካዩ ቢጫ ካርድም ተመልክቷል።
"ለካፍ እና ለፊፋ ደብዳቤ እንጽፋለን። መጀመሪያ ጨዋታው እንዴት እንደተካሄደ እንዲመረመር፤ ሲቀጥል አንዳንድ ውሳኔዎችን ለመቃወም ነው" ሲሉ የሳፋ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቴቦጎ ሞትላንቴ ተናግረዋል።
"ከጨዋታው በኋላ እንዳደረግነው መደበኛ ቅሬታ እንደምናቀርብ ለጨዋታው ኮሚሽነር አስመዝግበናል" ብለዋል።

በኳታሩ ዓለም ዋንጫ ተሳታፊ እንደሚሆኑ የተለዩ አገራትን ለመመልከት ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ ይጫኑ። ለኳታር የዓለም ዋንጫ የትኞቹ አገራት አለፉ? እነማንስ የማለፍ እድል አላቸው?

ሞትላንቴ እንዳሉት ሳፋ ጨዋታውን በመሩት ሴኔጋላዊያን በተለይም በመሃል ዳኛው ማጉዌት ንዳዬ ውሳኔው እና ሕጋዊነት ላይ ያሳስበዋል።
"በድርጊታቸው በጣም ተስፋ ቆርጠናል። ተጫዋቾቹን እንዲጎዱ አንፈቅድም። የመሞገት ዕድል ስናገኝ እንሞግታለን" ሲሉ አክለዋል።
"የፍጹም ቅጣት ምቱ ክስተት ብቻ ስላልሆነ እንደተዘረፍን ይሰማናል። በጨዋታው ዳኞች ብዙ አጠያያቂ የሆኑ ውሳኔዎች በመወሰናቸው ባለሙያ አናግረን ጠንከር ያለ ክስ ማቅረብ እንችላለን።"
ደቡብ አፍሪካ በ2018 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ወቅት አንድ ዳኛ በጨዋታ ማጭበርበር ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ከሴኔጋል ጋር ያደረጉት ጨዋታ በድጋሚ እንዲካሄ በመገደዳቸው ጨዋታዎችን የመድገም አቅም እንዳላቸው ደቡብ አፍሪካ ጠንቅቃ ታውቃለች።
ደቡብ አፍሪካ በመጀመሪያ ሴኔጋልን 2-1 አሸንፋ ነበር። ጋናዊው ዳኛ ጆሴፍ ላምፕቴይ 'የተወሰኑ ውርርዶችን ስኬታማ ለማድረግ በትንሹ የጎል ብዛት እንዲኖር ሁለት የተሳሳቱ ውሳኔዎችን በግልጽ ወስነዋል' ሲል ፊፋ ደምድሟል።
ይህም ሴኔጋላዊው ካሊዱ ኩሊባሊ በቴሌቭዥን ምልሰት ኳሱን በጉልበቱ መንካቱ ተደጋግሞ ቢታይም በእጁ ነክቶታል በሚል ለባፋና ባፋናዎች የፍጹም ቅጣት ምት መሰጠቱን ይጨምራል።
ፊፋ ያልተለመደ ውሳኔ በመስጠት ጨዋታው በድጋሚ እንዲካሄድ አዘዘ። ደቡብ አፍሪካ 2-0 ተሸንፋ ሩሲያ ላስተናገደችው የዓለም ዋንጫ ሴኔጋል ማለፏን አረጋግጣ ነበር።
"ፊፋ ከሴኔጋል ጋር ድጋሚ እንድንጫወት ያዘዘበትን ሁኔታ እየተመለከትን ነው። እናም ፍትሕ መሰጠት ካለበት በዚህ የጋና ጨዋታ ላይ ተመሳሳይ ውሳኔ ሊወሰድ ይገባል ብለን እናስባለን" ብለዋል ሞትላንቴ።












