የኳታር ዓለም ዋንጫ፡ የትኞቹ አገራት አለፉ? እነማንስ የማለፍ እድል አላቸው?

በአውሮፓውያኑ 2022 በኳታር ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ውድድሮች ባለፈው ሳምንት ሲካሄዱ ነበር።
ጥቂት የማይባሉ አገራት ከወዲሁ በዓለም ዋንጫው መሳተፋቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በሚቀጥሉት ወራት በሚደረጉ ጨዋታዎች ይለያሉ።
የአፍሪካ አገራት በ10 ምድቦች ተደልድለው በደርሶ መልስ ጨዋታቸውን ሲያከናውኑ ነበር።
እንደ ሴኔጋል ያሉ አገራት ቀድመው ማለፋቸውን ማረጋገጥ ቢችሉም ከየምድባቸው ያለፉት 10 አገራት ትናንት ምሽት በተደረጉ ጨዋታዎች እንዲሁም ዛሬና ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይለያሉ።
እነዚህ ከየምድቦቹ የሚያልፉት 10 አገራት በመጪዎቹ ወራት በሚያደርጓቸው የደርሶ መልስ ጨዋታዎች አምስቱ በቀጥታ ወደ ኳታር የዓለም ዋንጫ ማለፋቸውን ያረጋግጣሉ።
ከምድብ አንድ አልጄሪያ በ13 ነጥብ አንደኛ ስትሆን ቡርኪና ፋሶ በ11 ነጥብ ትከተላታለች። በዚህ ምድብ ነገ አልጄሪያ ከቡርኪና ፋሶ የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ በጉጉት ተጠባቂ ሆኗል። አሸናፊው አገር በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ ይገባል ማለት ነው።
በምድብ ሁለት ቱኒዚያና ኢኳቶሪያል ጊኒ በአምስት ጨዋታ በተመሳሳይ 10 ነጥብ አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ተቀምጠዋል። ነገ ምሽት ቱኒዚያ ከዛምቢያ እንዲሁም ኢኳቶሪያል ጊኒ ከሞሪታኒያ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ሁለቱም የማለፍ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
በምድብ ሦስት ደግሞ ናይጄሪያ ከ5 ጨዋታ 12 ነጥቦችን በመሰብሰብ አንደኛ ስትሆን ኬፕ ቬርዴ በ10 ነጥብ ትከተላታለች። ነገ ምሽት ሦስት ሰዓት ላይ ሁለቱ አገራት የሚገናኙ ሲሆን አሸናፊው በቀጥታ ያልፋል። አቻ የሚወጡ ከሆነ ደግሞ ናይጄሪያ ማለፏን ታረጋግጣለች።
አይቮሪ ኮስትና ካሜሩን የሚገኙበት ምድብ አራት እስከ መጨረሻው ጨዋታ ድረስ አጓጊ ነው። ምድቡን አይቮሪ ኮስት በ13 ነጥብ ስትመራ ካሜሩን ደግሞ በ12 ትከተላታለች።
ነገ ምሽት አራት ሰዓት ላይ እነኚህ በአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ ስም ያላቸው አገራት ይፋለማሉ። አቻ መውጣት ለአይቮሪ ኮስት በቂዋ ሲሆን ካሜሩን ግን የግድ ማሸነፍ አለባት።
በምድብ አምስት ደግሞ ማሊ ከስድስት ጨዋታ 16 ነጥብ በመሰብሰብ ወደ ጥሎ ማለፉ መቀላቀሏን ያረጋገጠች ሲሆን፤ በምድብ ስድስትም ቢሆን ግብፅ በተመሳሳይ ከ5 ጨዋታ 11 ነጥብ በመሰብሰብ ወደ ቀጣዩ ጥሎ ማለፍ ገብታለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ ሰባት ጋና እና ደቡብ አፍሪካ እስከ መጨረሻው ተናንቀው የቆዩ ቢሆንም፤ ትናንት ምሽት ባደረጉት ጨዋታ ጋና አንድ ለባዶ አሸነፋለች። በዚህም ጋና ጥሎ ማለፉን መቀላቀል ችላለች።
ምድብ ስምንትን ሴኔጋል በበላይነት ጨርሳለች። ከስድስት ጨዋታ 16 ነጥቦችን በመሰብሰብ በአስገራሚ አቋም የምድቡን ድልድል አሸንፋለች።
በምድብ ዘጠኝም ቢሆን ሞሮኮ ከአምስት ጨዋታ 15 ነጥብ በመሰብሰብ አንድ ጨዋታ እየቀራት በበላይነት መጨረሷን አረጋግጣለች።
በምድብ አስር ደግሞ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ከስድስት ጨዋታ 11 ነጥብ በመሰብሰብ በአንደኛነት አጠናቃለች።
ከአውሮፓ ምድብ ሰባት አገራት ከወዲሁ በኳታር ዓለም ዋንጫ መሳተፋቸውን አረጋግጠዋል። አገራቱም ቤልጂየም፣ ክሮሺያ፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሰርቢያ እና ስፔን ናቸው።
በዚህ ምድብ 13 አገራት ወደ ዓለም ዋንጫው የሚያልፉ ሲሆን ቀሪዎቹ አገራት ዛሬና ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች እንዲሁም በደርሶ መልስ ጨዋታዎች የሚታወቁ ይሆናል።
ዛሬ ምሽት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል በምድብ ሦስት ስዊዘርላንድ ከቡልጋሪያ እንዲሁም ጣልያን ከሰሜን አየርላንድ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት የሚጠበቁ ናቸው።
ምድቡን ጣልያን በ15 ነጥብ ስትመራ ስዊዘርላንድም በተመሳሳይ 15 ነጥብ ሁለተኛ ላይ ትገኛለች። ሁለቱም አገራት የማለፍ ዕድል ያላቸው ሲሆን የዛሬ ምሽቱ ጨዋታ የመጨረሻውና ወሳኙ ነው።
በምድብ ሰባት ደግሞ ኔዘርላንድስ፣ ቱርክ እና ኖርዌይ ተፋጠዋል።
ኔዘርላንድስ በ20 ነጥብ አንደኛ፣ ቱርክ በ18 ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም ኖርዌይ በተመሳሳይ 18 ነጥብ ሦስተኛ ላይ ናቸው። ነገ በሚደረጉት የዚህ ምድብ የመጨረሻ ዙር ጨዋታዎች ኔዘርላንድስ ከኖርዌይ እንዲሁም ቱርክ ከሞንቴኔግሮ ይገናኛሉ።
በምድብ ዘጠኝ እንግሊዝ እና ፖላንድ እስከመጨረሻው የምድብ ጨዋታ ድረስ አንገት ለአንገት ተያይዘው ቀጥለዋል። እንግሊዝ 23 ነጥብ ያላት ሲሆን ፖላንድ በ20 ትከተላለች።
ዛሬ ምሽት ፖላንድ ከሀንጋሪ እንዲሁም እንግሊዝ ከሳን ማሪኖ የሚያደርጉት ፍልሚያ በጉጉት የሚጠበቅ ነው።
ከደቡብ አሜሪካ ማለፍ የሚችሉት አራት ወይም አምስት አገራት ሲሆኑ ከወዲሁ ማለፏን ያረጋገጠችው ግን ብራዚል ብቻ ናት።
የማለፍ ተስፋ ካላቸው አገራት መካከል አርጀንቲና፣ ኢኳዶር፣ ቺሊ፣ ኡራጓይ እና ኮሎምቢያ ተጠቃሽ ናቸው።
ከሰሜን እና ማዕከላዊ አሜሪካ እንዲሁም ካሪቢያን አገራት ሦስት ወይም አራት ማለፍ የሚችሉ ሲሆን እስካሁን ግን የትኛውም አገር ማለፉን አላረጋገጠም።
ነገር ግን ምድቡን አሜሪካ በ14 ነጥብ እየመራች ሲሆን ሜክሲኮ በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጣ ሁለተኛ ላይ ትገኛለች። ካናዳ እና ፓናማም ቢሆኑ የማለፍ እድል አላቸው።
በእስያ ምድብ አምስት ወይም ስድስት አገራት ለኳታሩ ዓለም ዋንጫ እንደሚያልፉ ይጠበቃል። ነገር ግን በዚህ ምድብ እስካሁን ከአዘጋጇ ኳታር በስተቀር ተሳትፎውን ማረጋገጥ የቻለ አገር የለም።
ኢራን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሊባኖስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ አውስትራሊያ እና ጃፓን ሁሉም የማለፍ እድል አላቸው።












