ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚረዳ አዲስ ዓለም አቀፍ ስምምነት በግላስጎው ተደረሰ
አደገኛ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚረዳ ስምምነት በስኮትላንድ ግላግስጎው እየተካሄደ በሚገኘው የኮፕ26 ስብሰባ ላይ ተደርሷል።
የግላስጎው የአየር ጸባይ ስምምነት የከሰል ምርትን ለመቀነስ የተደረገ በአይነቱ የመጀመሪያው የተባለለት ሆኗል።
ከዚህ በተጨማሪም ስምምነቱ ጎጂ ጋዞችን መልቀቅ በፍጥነት እንዲቆምና በማደግ ላይ ለሚገኙ አገራት የአየር ጸባይ ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችላቸው ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መታሰቡን ያሳያል።
ይህ ስምምነት በሚደረግበት የመጀመሪያዎቹ ቀናት የከሰል ምርትን ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት የቀረበው ሀሳብ በሕንድ መሪነት ትልቅ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።
የሕንዱ የአየር ንብረት ሚኒስትር ብሁፔንደር ያዳቭ በስብሰባው ወቅት ድሃ አገራት ድህነትን ለመቀነስና የእድገት ጎዳናቸውን ለማሳለጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዴት አድርገው ከከሰል ሌላ አማራጭ ኃይል መጠቀም ይችላሉ በማለት ጠይቀዋል።
በመጨረሻም አገራት የከሰል ምርትን ሙሉ ለሙሉ ለማቆም የሚለውን ሀሳባቸውን በመተው ቀስ በቀስ በጊዜ ብዛት የከሰል ምርትን መቀነስ በሚለው ሀሳብ ተስማምተዋል።
ፖላንድ፣ ቬትናም እና ቺሊን ጨምሮ ዋና ዋና የከሰል ተጠቃሚዎች በኮፕ26 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ እንደ ከሰል፣ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ የኃይል ምንጮችን ላለመጠቀም ቃል ገብተዋል።
እንደ አውስትራሊያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና አሜሪካ ያሉ አንዳንድ በከሰል ላይ ጥገኛ የሆኑ ቀዳሚ ሃገራት ግን ቃል ከመግባት ተቆጥበዋል።
ስምምነቱን ከ40 በላይ ሃገራት ፈርመዋል። ፖላንድ፣ ቬትናም እና ቺሊ ለመጀመሪያ ጊዜ የድንጋይ ከሰል ኃይል ላለመገንባት እና በዘርፉ መዋለ ንዋይ ላለማፍሰስ ከተስማሙ 18 ሃገራት መካከል መሆናቸውን እንግሊዝ ገልጻለች።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የከሰል አጠቃቀምን በመቀነስ ረገድ መሻሻል ቢታይም በአውሮፓውያኑ 2019፣ 37 በመቶ የሚሆነውን የአለም ኤሌክትሪክ ከዚሁ ኃይል ምንጭ ይገኛል።
የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው ይሄኛው የግላስጎው ኮፕ26 ስብሰባ የአየር ጸባይ ለውጥን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት የመጀመሪያ መነሻ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።
'' በሚቀጥሉት ዓመታት አሁንም መሰራት የሚገባቸው በርካታ ስራዎች ይጠብቁናል። ነገር ግን ዛሬ ላይ የደረስንበት ስምምነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ ስጋቶችን ለመቅረፍ በምናደርገው ጥረት ትልቅ እርምጃ ነው። የከሰል ምርትን መቀነስና የዓለማችን ሙቀት ከ1.5 ሴልሺየስ ከፍ እንዳይል ማድረግ ላይ መስማማትችን ትልቅ ማሳያ ነው'' ብለዋል።
የእሜሪካው የአየር ንብረት ተወካይ ጆን ኬሪ ደግሞ የግላስኮው ኮፕ26 ስምምነት ችግሩን የሚቀርፍ ሳይሆን ወደፊት ለሚጠብቁን በርካታ ስራዎች መነሻ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፈሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ዓለማችን አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ትገኛለች ብለዋል። '' በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጣ ትልቅ ቀውስ እንዲከሰት እያደረግን ነው። በፍጥነት ውሳኔ ላይ ደርሰን ምድራችንን የምንታደግበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል''
በስምምነቱ መሰረት አገራት በሚቀጥለው ዓመት ተሰባስበው በካርቦን ልቀት ላይ ያላቸውን አስተዋጽኦ ለመቀነስ ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ የሚጠበቅ ሲሆን የምድርን ሙቀትም ለመቀነስ ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም ከስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሏል።
የዓለም ሙቀት ከ1.5 ሴልሺየስ በላይ ከፍ የሚል ከሆን ምድራችን አይታው የማታውቀው አይነት ቀውስ እንደምታስተናግድ ተመራማሪዎች ያሳሰቡ ሲሆን በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎችም ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ይወድቃሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በኮፕ26 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር በሚደረገው ትግል ውስጥ ወጣቶች "ቁጣቸውን እንዲገልጹ" ጥሪ አቅርበዋል።
ለውጥ እንዲመጣ ከፈለጉም የፖለቲካ ጫና እንዲያደርጉ አሳስበዋቸዋል። ሆኖም በሂደቱ ስምምነትን መቀበል እንደሚኖርባቸው አስጠንቅቀዋል።
የቀድሞ ፕሬዝዳንቱ አክለውም የቻይናን እና የሩሲያ መሪዎች በኮፕ26 ስብሰባ ላይ በአካል ስላልተገኙ ወቅሰዋቸዋል። ኦባማ አብዛኛው ንግግራቸው ለወጣት አንቂዎች የታለመ ሲሆን "መበሳጨታቸው ትክክል ነው" በማለት ተናግረዋል።
በቀጥታ ለወጣቶች ንግግር ሲያደርጉም "ፖለቲካን ችላ ማለት አይችሉም" ያሉ ሲሆን ተቃውሞ እና ሃሽታግ ግንዛቤን የሚያሳድጉ ሲሆን በተወሰነ ደረጃም ወደ ፖለቲካው መግባት አለባቸው ብለዋል።
"ደስተኛ መሆን ላይሆኑ ይችላሉ ነገር ግን ችላ ማለት አያዋጣም። ለፖለቲካ በጣም ንጹህ መሆን አይቻልም።"
የሴት ልጆቻቸውን የግብይት ልማዶች በመጥቀስ ወጣቶች ለአየር ንብረት ቁርጠኛ የሆኑ የንግድ ሥራዎችን እንዲደግፉ ያልሆኑትንም ደግሞ እንዲተዉ ጠይቀዋል።
በዚህ የኮፕ26 ስብሰባ ላይ ሌላ ያልተለመደ ነገርም ተስተውሏል። ቻይና እና አሜሪካ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት በአየር ጸባይ ለውጥ ዙሪያ ተባብረው ለመስራት መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል።
በዓለማችን ከፍተኛውን የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት የሚያደርጉት አሜሪካ እና ቻይና ከዚህ በኋላ በጋራ ለመስራት ነው የተስማሙት።
የስምምነት ሰነዱም ከዚህ በፊት የነበራቸውን አብሮ የመስራት ሂደት በተጠናከረ ሁኔታ በማስቀጠል በፓሪስ በተደረሰው ስምምነት መሰረት 1.5 ሴልሺየስ ቅዝቃዜ ግብ ላይ ለመድረስ መታቀዱን ያሳያል።
የቻይና ከፍተኛ የአየር ንብረት ተደራዳሪ የሆኑት ዢ ዤንሁዋ ለተሰበሰቡጋዜጠኞች ሲናገሩ '' በቻይና እና አሜሪካ መካከል ካለው ልዩነት በበለጠ ስምምነት አለ'' ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የቻይናው አቻቸው ሺ ዢን ፒንግ ደግሞ በሚቀጥለው ሳምንት በበይነ መረብ አማካይነት እንደሚወያዩ ይጠበቃል። እነኚህ ሁለት አገራት በዓለማችን በበርካታ ጉዳዮች ቁልፊ ሚና ያላቸው ናቸው።
ረቡዕ ዕለት ባልተለመደ መልኩ ሁለቱ አገራት በጋራ ስምምነታቸውን የገለጹ ሲሆን ከመስማማታቸው በፊት ግን በተለይ የሚቴን ልቀት፣ ወደ ንጹህ ኃይል መሸጋገር እና ካርቦንን የማጥፋት ሂደት ላይ ከፍተኛ ውይይት በማድረግ ነው እቅዳቸውን ይፋ ያደረጉት።
ነገር ግን ቻይና የሚቴን ልቀትን ለመቀነስ አገራት የተስማሙበትን ሰነድ አልቀበለውም ብላለች።
ይህ ጋዝ ለግሪንሃውስ መሸንቆር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው። ይህ ሚቴንን ለመቀነስ የተደረገውን ስምምነት እስከ 100 የሚደርሱ አገራት የፈረሙበት ሲሆን ቻይና ግን በአገር ደረጃ የራሴን የሚቴን ጋዝ ልቀት የሚቆጣጠር እቅድ አዘጋጃለሁ ብላለች።
አገራቱ አክለውም ይህንን ግብ ለማሳካት እንቅፋት የሆኑ ማነቆዎችን በማስወገድ ተባብረው ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድና የአየር ጸባይ ነውጥን ለመከላከል ቆርጠናል ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎች እንደሚሉት የዓለም ቅዝቃዜ ከ1.5 ሴልሺየስ ከፍ እንዳይል ማድረግ ከተቻለ የሰው ልጅ ከባዱን የአየር ንብረት ጫና መቋቋም ይችላል።
ይህ ደግሞ የሰው ልጅ በኢንዱስትሪዎች ማምረት ካልጀመረበት ዓመታት ጋር የሚመሳሰል ይሆናል ማለት ነው።
በአውሮፓውያኑ 2015 በፈረንሳዩዋ ዋና ከተማ ፓሪስ በተደረገው የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ላይ የዓለም መሪዎች የበካይ ጭሶችን መጠን በመቀነስ የዓለም ሙቀት እንዳይጨምር ለመስራት ቃል ገብተው ነበር።
የስዊዘርላንድ የአየር ንብረት ሚኒስትር የሆኑት ሲሞንታ ሶማሩጋ በበኩላቸው '' የከሰል ምርትን እንደ ዋነኛ የኃይል ምንጭ ላለመጠቀም የቀረበው ሃሳብ ተሸርሽሮ መቀነስ በሚለው ብቻ በመተካቱ ማዘናችንን ልገልጽ እወዳለሁ'' ብለዋል። '' የምድርን ሙቀት ከ1.5 ሴልሺየስ ከፍ እንዳይል ለምናደርገው ጥረት ይህ ውሳኔ አይጠቅምም። እንደውም ስራችንን በጣም ከባድ ያደርገዋል'' ሲሉ ተደምጠዋል።
የከሰል ምርት በምድራችን ለሚለቀቀው የካርቦንዳይኦክሳይድ 40 በመቶ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሲሆን የምድርን ሙቀት ከ1.5 ከፍ እንዳይል በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። በአውሮፓውያኑ ፓሪስ ላይ በተካሄደው ስብሰባ ላይ የከሰል ምርትን በ2030፣45 በመቶ ለመቀነስ እቅድ ተይዟል። በ2050 ደግሞ ሙሉ በሙሉ የከሰል ምርትን ለማስቀረት አገራት እቅድ አስቀመጥዋል።
ይህንን እቅድ ስኬታማ ለማድረግ ደግሞ እንደ እንቅፋትነት ከሚጠቀሱት መካከል ያደጉት አገራት ድሃ አገራትን ለመደገፍና አማራጭ የኃይል መንገዶችን ለመደገፍ የሚያደርጉት የገንዘብ እርዳታ ላይ መስማማት አለመቻላቸው ነው። በአውሮፓውያኑ 2009 ያደጉት አገራት እስከ 100 ቢሊየን ዶላር ድረስ ፈሰስ ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር።
ይህ ገንዘብ ባሳለፍነው ዓመት መለቀቅ የነበረበት ቢሆንም እስካሁን ድረስ ግን ቃል የተገባው ገንዘብ አልተገኘም።
ተመራማሪዎች እንደሚሉት አገራት የገቡትን ቃል ለመፈጸም ቸልተኝነት ባሳዩ ቁጥር ከባድና ተደጋጋሚ ጎርፎች፣ በረሃማነት እንዲሁም ያልተለመደ ቅዝቃዜ እየጨመረ ይሄዳል።