ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግብጽ፡ አስዋን ውስጥ ጊንጦች ሶስት ሰዎችን ገድለው በመቶዎች የሚቆጠሩ አቆሰሉ
በግብጽ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው አስዋን ከተማ ውስጥ ጊንጦች ለሶስት ሰዎች ሕይወት ማለፍና በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳት ምክንያት መሆናቸው ተሰምቷል።
እስከ 450 የሚደርሱ ሰዎች በጊንጥ ተነድፈው ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ይህ ክስተት በተደጋጋሚ እንደሚያጋጥም የአገሪቱ የጤና ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ግብጽ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት ጊንጦች ወደ መንገዶች ተገፍተው የሚመጡ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ወደ ሰዎች መኖሪያ ቤት ይገባሉ።
በያዝነው ሳምንት አርብ ዕለት በአካባቢው በሚገኘው ወንዝ አቅራቢያ የጣለው ከባድ ዝናብ ከሌሎች ጊዜዎች ጠንከር ያለ ነበር ተብሏል።
ይህን መሰል ከባድ ዝናብ ሲያጋጥም ደግሞ ጊንጦች በውሀው እየተገፉ ወደ ጎዳናዎች የሚወጡ ሲሆን እባቦችም ቢሆን አካባቢያቸው ስለሚረበሽ መጠለያ ፍለጋ ይንቀሳቀሳሉ።
አል አህራም ለተባለው የዜና ወኪል አንድ የአካባቢው የጤና ኃላፊ እንደገለጹት በተራራማ እና በረሀማ አካባቢዎች ለሚገኙ መንደሮች ተጨማሪ ጸረ መርዝ መድሀኒቶች እንዲከፋፈሉ እየተደረገ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ክትባቶችን ለመስጠት ተሰማርተው የነበሩ የህክንማ ባለሙያዎች ትኩረታቸውን በጊንጥ ለተነደፉ ሰዎች እርዳታ መስጠት ላይ እንዲያደርጉ መገደዳቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።
በነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችም ከቤታቸው እንዳይወጡና ዛፎች የሚበዙባቸው ቦታዎችን እንዳያዘወትሩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
ግብጽ በዓለማችን ገዳይ የሚባሉ ጊንጦች የሚገኙባት አገር ስትሆን የእነዚህ ጊንጦች መርዝ አንድን ሰው ከአንድ ሰአት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የመግደል አቅም አላቸው።