ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩዋንዳዊው 'ዩቲዩበር' ባለሥልጣናትን በማዋረዱ በእስር ተቀጣ
ሩዋንዳዊው ታዋቂ ዩቲዩበር መንግሥትን በመተቸቱ የሰባት ዓመት እስር ተፈረደበት።
ዲዩዶኔኔ ኒዮንሴንጋ፣ በቅፅል ስሞቹ 'ሲዩማ' ወይም 'አይረን' በመባል የሚታወቀው ዩቲዩበር በማጭበርበር፣ በማስመሰል እና የመንግሥት ባለሥልጣናትን በማዋረድ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።
ግለሰቡ የቀረበበትን ክስ ውድቅ ያደረገ ሲሆን ይግባኝ እንደሚጠይቅም አስታውቋል።
በዩቲዩብ የወጡት ቪዲዮዎቹ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በነበረው የእንቅስቃሴ ገደብን በመጠቀም የአገሪቱ ወታደሮች በዝቅተኛ መንደሮች ላይ የሚኖሩ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የመብት ጥሰት አድርሰዋል ሲል ከሷቸዋል።
ሌላው ታዋቂ ዩቲዩበር እንዲሁ በቅርቡ ሁከትን በማነሳሳት የ15 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።
የሩዋንዳ ባለሥልጣናት የተቃዋሚዎችን ድምፅ በማፈን እና መንግሥትን የሚተቹትን በማሰር በርካታ ክሶች ይቀርብባቸዋል።
ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በሩዋንዳ የተከሰተውን የዘር ፍጅት ተከትሎ ሥልጣን ጨብጠው አሁን ድረስ አገሪቱን በፕሬዝዳንት እመሩ የሚገኙት ፖል ካጋሜ፤ በአገሪቱ ከፍተኛ መረጋጋትና ምጣኔ ሀብታዊ እመርታን በማስመዝገብ ቢወደሱት በመብት አከባበር በኩል ይተቻሉ።
የአስተዳደራቸው ተቃዋሚ የሆኑ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን በማሳደድና የተቃውሞና የትችት ድምጾችን በማፈን በተደጋጋሚ ሲከሰሱ ቆይተዋል።