ወጣቶች በአየር ንብረት ዙሪያ ቁጣቸውን እንዲገልጹ ኦባማ ጠየቁ

ባራክ ኦባማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ባራክ ኦባማ በኮፕ26 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ በሚደረገው ትግል ወጣቶች "ቁጣቸውን እንዲገልጹ" ጥሪ አቅርበዋል።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለውጥ እንዲመጣ የፖለቲካ ጫና እንዲያደርጉ አሳስበዋቸዋል። ሆኖም በሂደቱ ስምምነትን መቀበል እንደሚኖርባቸው አስጠንቅቀዋል።

ኦባማ የአየር ንብረት አደጋን ለማስቀረት ዓለም "ወደምንፈልጋት ቦታ አልደረሰችም' ብለዋል።

የዶናልድ ትራምፕን "የአየር ንብረት ሳይንስ ላይ የከፈቱትን ዘመቻ" ተችተው አሁን አሜሪካ ከፊት ሆና ለመምራት ዝግጁ ነች ብለዋል ።

የቻይናን እና የሩሲያ መሪዎች በኮፕ26 ስብሰባ ላይ በአካል ስላልተገኙ ኦባማ ወቅሰዋቸዋል።

ኦባማ በግላስጎ ንግግር ለማድረግ ወደ መድረክ ሲወጡ እና በንግግራቸው መጨረሻ ላይ ደማቅ ጭብጨባ ተደርጎላቸዋል። ነገር ግን ከአንቂዎችም ግፊት ነበር።

እሳቸው ኋይት ሃውስ በነበሩበት በአውሮፓውያኑ 2015 የተደረሰው የፓሪስ ስምምነት የተገባው ቃል ባለማሟላቱ ሃገራትን ጠይቀዋል።

ሆኖም አንቂዎች በእራሳቸው አስተዳደር ያልተሠሩትን በፍጥነት ጠቁመዋል። ያደጉት ሃገራት የአየር ንብረት ፋይናንስ 100 ቢሊዮን ዶላር በዓመት ለድሃ ሀገራት ለመስጠት የገቡትን ቃል አለመሳካቱን እንደማሳያ አንስተዋል።

ምናልባትም ስላሉበት ቦታ እርግጠኛ የማይመስሉት ኦባማ "ኤመራልድ አይልስ" ውስጥ መገኘታቸውን ጠቅሰዋል። ኤመራልድ ኤይል በግጥም ስለምትታወቀው አየርላንድ የተሳሳተ ማጣቀሻ ይመስላል። እንግሊዛዊውን ሼክስፒርንም አንስተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን ተፅእኖ ለመቀነስ አሁንም ብዙ ከባድ እና የተዘበራረቀ ሥራ እንዳለ አምነዋል። እሳቸው በግንባር ቀደምትነት እገዛ ካደረጉለት የፓሪስ ስምምነት በኋላ ባሉት ስድስት ዓመታት አንዳንድ ተስፋ ሰጪ መሻሻሎች ታይተዋል ብለዋል።

"ፖለቲካን ችላ ማለት አይችሉም"

ኦባማ አብዛኛው ንግግራቸው ለወጣት አንቂዎች የታለመ ሲሆን "መበሳጨታቸው ትክክል ነው" በማለት ተናግረዋል።

በቀጥታ ለወጣቶች ንግግር ሲያደርጉም "ፖለቲካን ችላ ማለት አይችሉም" ያሉ ሲሆን ተቃውሞ እና ሃሽታግ ግንዛቤን የሚያሳድጉ ሲሆን በተወሰነ ደረጃም ወደ ፖለቲካው መግባት አለባቸው ብለዋል።

"ደስተኛ መሆን ላይሆኑ ይችላሉ ነገር ግን ችላ ማለት አያዋጣም። ለፖለቲካ በጣም ንጹህ መሆን አይቻልም።"

የሴት ልጆቻቸውን የግብይት ልማዶች በመጥቀስ ወጣቶች ለአየር ንብረት ቁርጠኛ የሆኑ የንግድ ሥራዎችን እንዲደግፉ ያልሆኑትንም ደግሞ እንዲተዉ ጠይቀዋል።

የኦባማ ዋናው ንግግር ወጣት አንቂዎችን "ተናደዱ" ማለታቸው ነበር።

" ወጣቶች ሁሉ - እንድትናደዱ እፈልጋለሁ። በብስጭት እንድትቆዩ እፈልጋለሁ" ብለዋል።

"ነገር ግን ያንን ቁጣ ለዓላማችሁ ማሳኪያ ተጠቀሙበት:: ያንን ብስጭት ታጠቁ:: ለበለጠ ውጤት ጠንክሮ መግፋቱን ቀጥሉበት:: ምክንያቱም ፈተናውን ለመወጣት የሚያስፈልገው ይህ ነው:: ራስህን ለማራቶን እንጂ ለአጭር ርቀት አታዘጋጅ::"

"ከድንበር ተሻግረው እንቅስቃሴ እየፈጠሩ" ያሉ እንደ ግሬታ ተንበርግ ያሉ አንቂዎችን አመስግነው ወጣቶች ቢያንስ ለአየር ንብረት ለውጥ የሚቆሙ ፖለቲከኞችን እንዲመርጡ አሳስበዋል።

"ህይወታችሁ በእሱ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ አስባችሁ ድምጽ ስጡ" ብለዋል።

ከአሜሪካ በኩል የነበረው ተቃውሞ'

በትራምፕ አስተዳደር ወቅት ለአራት ዓመታት ያህል በዩናይትድ ስቴትስ ከነበሩት የፖለቲካ ልዩነቶች እና ሃገሪቱ ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጥረቶች ብትቀርም አሁን ወደ መስመሩ ተመልሳለች ብለዋል። ለውጥ ለማድረግም ቁርጠኛ መሆኗን የቀድሞው ፕሬዝዳንት አጥብቀው ተናግረዋል ።

ኦባማ የአየር ንብረት ለውጥን "ማጭበርበሪያ" ሲሉ በገለጹት የሪፐብሊካኑን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዙሪያ ብዙ ሃሳብ ሰንዝረዋል። ትራምፕ ሥልጣን ሲይዙ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት አወዛጋቢ በሆነ መንገድ ወጥተዋል። አሜሪካ በጆ ባይደን አስተዳደር ወደ ስምመነቱ ተቀላቅላለች።

የአየር ንብረት ለውጥን በቁም ነገር የሚመለከቱ ሪፐብሊካኖች "ብርቅዬ ናቸው" ብለዋል። ይህ የሪፐብሊካኖች የልዑካን ቡድን በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የተሳተፈበት የመጀመሪያ ዓመት ነው።

ኦባማ በአየር ንብረት ቀውሱ ላይ ለደረሰው የዓለም አቀፍ ግንኙነት መፈራረስ የኮሮና ወረርሽኝን፣ የአሜሪካ ብሔርተኝነት መጨመርን እና የትራምፕ አስተዳደር ትብብር ማነስን ተጠያቂ አድርገዋል።

በሩስያ እና በቻይና ላይ ትችት የሰነዘሩት ኦባማ "የሁለቱ ታላላቅ የዓለም በካይ ጋዝ ለቃቂ ሃገራት" መሪዎች በአየር ንብረት ጉባኤው በአካል አለመገኘታቸው "ተስፋ አስቆራጭ ነው" ብለዋል።

በጉባዔው ላይ ከ 120 በላይ መሪዎች ተገኝተዋል። ወረርሽኙ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ዓለም አቀፍ ጉዞዎችን ያላደረጉት ቭላድሚር ፑቲን እና ዢ ጂንፒንግ በቪዲዮ ለመሳተፍ መርጠዋል ።

ኦባማ "አስጊ የሆነ ፍጥነት አልባነት" እያሳዩ ነው ብለዋል።

44ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የአየር ንብረት ለውጥን መዋጋት ከባድ እና የተዘበራረቀ ጠቅሰው "እያንዳንዱ ድል ያልተሟላ" እንደሚሆን ለህዝቡ በመንገር ንግግራቸውን ቋጭተዋል።

"የሰው ልጅ ከዚህ በፊት ከባድ ሥራዎችን ሠርቷል። እንደገና ከባድ ነገሮችን ማድረግ እንደምንችል አምናለሁ" ብለዋል።