ጆርጅ ክሎኒ መገናኛ ብዙኀን የልጆቹን ምስል እንዳይጠቀሙ ጠየቀ

ታትሟል

የሆሊውድ ፊልም ተዋናዩ ጆርጅ ክሎኒ ለመገናኛ ብዙኀን በጻፈው ግልጽ ደብዳቤ ላይ የልጆቹን ፊት የሚያሳይ ምስል እንዳይጠቀሙ ጠየቀ።

ክሎኒ በደብዳቤው ላይ እንደገለፀው እንዲህ ዓይነት ምስሎች በባለቤቱ የሥራ ጠባይ የተነሳ የልጆቹን ሕይወት አደጋ ላይ ይጥላል።

አማል ክሎኒ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ጠበቃ ስትሆን ጆርጅ ክሎኒ በደብዳቤው ላይ እንደገለፀው የሽብርተኛ ቡድን አባላትን ችሎት ፊት አቅርባ ትሞግታለች።

ተዋናይ ጆርጅ ክሎኒ ለመገናኛ ብዙኀን የጻፈው ደብዳቤ በበርካታ ጋዜጦች እና መጽሔቶች ላይ ታትሟል።

ግራቪቲ፣ ኦሽንስ ኢለቨን ላይ በመተወን ዝናንና አድናቆትን ያተረፈው ጆርጅ ክሎኒ፣ እርሱም ሆነ ባለቤቱ የማህበራዊ ሚዲያ እንደማይጠቀሙ እንዲሁም የልጆቻቸውን መብትና ደህንነት እንደሚጠብቁ ተናግሯል።

ክሎኒ ደብዳቤውን ለመጻፍ የወሰነው የአሜሪካዊቷ ተዋናይት ቢሊ ሎርድ የአንድ ዓመት ልጅ ምስል በድረ ገጽ ላይ ታትሞ ከተመለከተ በኋላ ነው።

ደብዳቤው በቀጥታ ፤ዴይሊ ሜል እና ሌሎች የሕትመት ውጤቶችን የተጻፈ ቢሆንም ዴይሊ ሜል ግን እስካሁን ድረስ ምላሽ አልሰጠም።

ከዚህ ቀደም የ60 ዓመቱ ተዋናይ፣ ሜይል ኦንላየን የተሰኘ ድረ ገጽ ስለ ባለቤቱ እናት ባሪያ አላሙዲን ሀሰተኛ ዘገባ ካሰራጨ በኋላ፣ የቀረበለትን የይቅርታ ጥያቄ አልቀበልም ማለቱ ይታወሳል።

ጆርጅ እና አማል ክሎኒ የተጋቡት እኤአ በ2014 ሲሆን እኤአ በ2017 መንታ ልጆችን ወልደዋል።

የደብዳቤው ሙሉ ቃል ምን ይላል?

"የቢሊ ሎርድ አንድ ዓመት ልጅ በድረ ገጽ ላይ ታትሞ ካየን በኋላ፣ በመቀጠልም ምስሉ ከድረ ገጹ ላይ በማጥፋታችሁ፣ የልጆቻችንን ምስል በሕትመት ስራዎቻችሁ ላይ ከመጠቀም እንድትቆጠቡ እንጠይቃችኋለን"

ጆርጅ ክሎኒ በሥራው ባህሪ የተነሳ በበርካታ ሕዝብ ዘንድ የሚታወቅ መሆኑን በመጥቀስ አንዳንድ ግዜ ተገቢ ያልሆኑ ምስሎቹ ሲወጡ በዝምታ መመልከቱን በመግለጽ " ልጆቻችን ግን እንዲህ ዓይነት ውለታ ውስጥ አልገቡም" ሲል ደብዳቤው ላይ አስፍሯል።

"የባለቤቴ ሥራ ከሽብርተኛ ቡድኖች ጋር እሰጥ አገባ ያለበት እንዲሁም ችሎት ፊት አቅርቦ መሞገትን ስለሚጨምር የቤተሰቦቻችንን ደህንንት ለመጠበቅ በተቻለን መጠን እንሞክራለን፤ ነገር ግን ማንኛውም የመገናኛ ብዙኀን ምስላቸውን የሚያትምና የሚያሰራጨው ከሆነ ያንን ማድረግ አንችልም" ብሏል።

"የልጆቻችንን ምስል ሸጠን አናውቅም፣ የማህበራዊ ሚዲያም ተጠቃሚ አይደለንም። ምስላቸውንም አጋርተን አናውቅም። ምክንያቱም ያንን ማድረግ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ስለሚጥለው ነው። እንዲሁ መሰረት የሌለው ስጋት ሳይሆን ተጨባጭ መሰረት ያለው፣ የከፋ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ስጋት ነው"

በመቀጠልም ክሎኒ የመገናኛ ብዙኀኑ ንፁኀን ዜጎችን የጥቃት ዒላማ እንዳይሆኑ ከማስታወቂያ ገቢያቸው ይልቅ እንደሚያስቀድሙ ያለውን እምነት ገልጿል።