ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኒጀር ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት 69 ሰዎች ተገደሉ
ታትሟል
የኒጀር መንግሥት እስላማዊ ታጣቂዎች ናቸው ተብለው በተጠረጠሩ አጥቂዎች ከ 69 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀን የሚቆይ ብሔራዊ የሐዘን ቀን አወጀ።
ጥቃቱ የተፈጸመው ኒጀርን ከማሊ በሚያዋስነው የደቡብ-ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ነው።
የአካባቢው ከንቲባ እና የሚሊሻ አደረጃጀት ኃላፊ በጥቃቱ ከተገደሉት ሰዎች መካከል ሲሆኑ፣ እስከ አሁን ድረስ ማክሰኞ ቀን ለተፈጸመው ለዚህ ጥቃት ኃላፊነት የወሰደ ቡድን የለም።
አጥቂዎቹ ከራሳቸው ቡድን የሞቱባቸውን ሰዎች አስከሬን በመያዝ ወደ ማሊ ድንበር መሸሻቸው ተነግሯል።
የኒጀር የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር እንደገለጹት በሟቹ ከንቲባ የሚመራው ልኡክ «ማንነታቸው ባልታወቀ ሽፍታዎች» ጥቃት እንደተከፈተበት ተናግረዋል።
አካባቢው ራሱን የእስላማዊ መንግሥት ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር ግንኙነት ካለው የሚሊሺያ ቡድን ቁጥጥር ስር እንቆየ ይነገራል። ኒጀር ከማሊ. ከቡርኪና ፋሶ እና ናይጄሪያ ጋር በሚያዋስኗት ድንበሮቿ ላይ ከጅሃዳዊ ቡድኖች በርካታ ጥቃቶችን እያስተናገደች ትገኛለች።
በአገሪቱ ደቡብ-ምዕራባዊ ክፍል ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ ከ500 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።