የተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አጸደቀ

ታትሟል

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት ተግባራዊ የሚሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጸደቀ።

ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት ጥቅምት 25፣ 2014 ዓ.ም ባካሄደውም 1ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ስብሰባው ነው ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለትን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያጸደቀው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የአስቸኳይ ጊዜ እንዲደነገግ ወስኗል።

ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ "በአገሪቱ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀኑ" እንደሆነና ይህንንም አደጋ "በመደበኛው የሕግ ሥርዓት መቆጣጠር ባለመቻሉ የአገሪቱን የፀጥታና የደኅንነት ተቋማትን እንዲሁም ዜጎችን በማቀናጀት የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ" ሕጋዊ ማዕቀፍ በማስፈለጉ መሆኑን በወቅቱ የፍትህ ሚኒስትሩ ተናግረው ነበር።

ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት የሚቆይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን አስፈላጊነቱ ታይቶ ለተጨማሪ አራት ወራት ሊራዘም እንደሚችል ተጠቁሟል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላት ለመሰየም የቀረበውን የውሳኔ ኃሳብ መርምሮ ለማፅደቅ እየተወያየ መሆኑም ተዘግቧል።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የሚያስፈጽምና በበላይነት የሚመራ አካል ይቋቋማል ተብሏል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአገሪቱ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የበላይነት የሚመራ ሲሆን ተጠሪነቱም ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆን ተገልጿል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመው አካል ሁሉንም የፀጥታ አካላት ማዘዝና ማንቀሳቀስ የሚችል ሲሆን በአገሪቱ የሚገኙ "ማንኛውንም መሳሪያ የታጠቀ አካል የማዘዝና የማሰማራት" ስልጣን ተሰጥቶታል ተብሏል።

ይህ አካል ሌሎች ዝርዝር የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣንና ኃላፊነቶች ተሰጡት ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሰዓት እላፊን ማወጅ፣ እንቅስቃሴዎችን መገደብ፣ በሽብር ከተፈረጀ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝና ተጠያቂ ማድረግ ይገኙበታል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው፤ በቀላሉ እስከ ሦስት ዓመት የሚቀጣ ሲሆን ከፍ ሲል ደግሞ እስከ 10 ዓመት በሚደርስ አስራት ሊቀጣ ይችላል።