ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮፕ26 ፡ ግሬታን ጨምሮ ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾች ግላስጎው ገቡ
በሺዎች የሚቆጠሩ ተሟጋቾች የአየር ንብረት ለውጥ ስጋታቸውን ለማሳወቅ በስኮትላንድ ትልቋ ከተማ ደረሱ።
ከተሟጋቾቹ መካከል ግሬታ ቱንበርግን ትገኝበታለች።
ግሬታ በባቡር ተሳፍራ ግላስጎው ስትደርስ በተመለከተቸው ነገር በድንጋጤ ተውጣ ነበር።
ስዊድናዊቷ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋች ግሬታ በከተማዋ ማዕከላዊ የባቡር ጣቢያ ስትደርስ በፖሊስ፣ በተሟጋቾች እና በመገናኛ ብዙኃን ተከባ ነበር።
እሁድ ከሚጀመረው የኮፕ26 ተቃውሞ ቀደም ብሎ ወደ ግላስጎው የሚጓዙ የሐይማኖት ቡድኖች በከተማዋ ተሰባስበዋል።
በርካቶች ዝግጅቱ ላይ ለመገኘት በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን በእግራቸው ነበር የተጓዙት።
ዝግጅቱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ ወቅት በግላስጎው እና በዓለም ዙሪያ ለማካሄድ ለታቀዱ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ነበር።
ግሬታ ተንበርግም ከለንደን ኢዩስተን ባበቡር ወደ ግላስጎው ያቀናችው "ፍራይደይስ ፎር ፊዩቸር" የሚል መፈክር ይዛ ነበር። 'ፍራይደይስ ፎር ፊዩቸር' እአአ በ2018 በትምህርት ቤቷ በተካሄደ አድማ በመነሳሳት የተሰጠ የወጣቶች እንቅስቃሴ ስያሜ ነው።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ የሲቪል እንቅስቃሴ ኤግስቲንክሽን ሬቤሊየን (ኤክስአር) እና የሐይማኖት ተጓዦች ቡድንም በግላስጎው ተሰባስበዋል።
በግላስጎው በሚገኘው የቅድስት ማርያም ኤፒስኮፓል ካቴድራል ደወሎች ከምሽቱ 4፡00 ላይ የሰው ልጆች ለአየር ንብረት ትኩረት እንዲሰጡ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።
ስለ አየር ንብረት ለውጥ ድምጻቸውን ለማሰማት ከተማዋ ከገቡት መካከል የስፔን የአየር ንብረት ተሟጋቾች ቡድን ማርቻ ግላስጎው ይገኙበታል። ይህ ቡድን ግላስጎው ለመድረው ከቢልባኦ ፖርተስማውዝ በመርከብ ተጎዞ ግላስጎው ለመድረስ ደግሞ 30 ቀናት በእግር ተጉዟል።
ካሚኖ ቱ ኮፕ26 አባላት ደግሞ ከለንደን እና ብሪስቶል ግላስጎው ለመድረስ ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ ፈጅቶባቸዋል።
የወጣት ክርስቲያን ክላይሜት ኔትወርክ ተሟጋቾችም ከኮርንዎል 1ሺህ 200 ማይል ርቀት በእግር በመጓዝ ቅዳሜ ዕለት ከተማዋ ደርሰዋል።
ኢኩሜኒካል የሐይማኖት ተጓዦችም ከፖላንድ፥ ስዊድን እና ጀርመን ግለስጎው የገቡ ሲሆን የኮፕ206 ሐይማኖታዊ ተጓዦችም ከደንበር ግላስጎው በእግር ተጉዘዋል።
ግላስጎው የሚገኙ አርቲስቶች ዞ ዎከር እና ኒል ብሮምዊችም የካፒታሊዝምን የሚያሳይ 30 ሜትር የሚረዝም ቅርጽ ከሐይማኖት ቡድኖች ጋር በመሆን አሳይተዋል።
በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት 30 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች የአየር ንብረት ጉባኤው ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የስኮትላንድ ፖሊስ ኣዛዥ ሌን ሊቪንግቶን ዝግጅቱን ለማወክ ጥረት የሚያደርጉ ካሉ የጸጥታ ኃይሉ አፋጣኝና የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል።
የጸጥታ ኃይሉ ከሌሎች የዩናይትድ ኪንግደም ክፍሎች ከመጡ 7ሺህ የፖሊስ መኮንኖች ጋር መሰማራታቸውንም የፖሊስ አዛዡ ገልጸዋል።
በሌሎቹ ከተሞች ትዕይንታዊ የሆኑ ተቃውሞዎች እየተካሄዱ ነው።