የሶቭየት ህብረት ፊት እና ድምፅ በመባል የሚታወቁት ዜና አንባቢ አረፉ

ኢጎር ኪሪሎቭ

የፎቶው ባለመብት, Tass via Getty Images

ታትሟል

የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ፊት እና ድምጽ በመባል የሚታወቁት የቴሌቪዥን ዜና አንባቢና አስተዋዋቂ ኢጎር ኪሪሎቭ በ89 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

የቀድሞው የቴሌቪዥን አንባቢ ህይወታቸው ያለፈው በሩሲያ ነው።

በተረጋጋና በሚስብ መልኩ ዜናን በማቅረብ የሚታወቁት ይህ ጋዜጠኛ በህዋ ውስጥ የነበረውን የመጀመሪያውን የስፑትኒክ ተልዕኮ ለተመልካቾች ያሳወቁበትን መንገድ ብዙዎች አይዘነጉትም።

በወቅቱ የነበረውንም የኮሚኒስት ፓርቲ መግለጫዎች በማቅረብ የወቅቱ ትውልድ ያስታውሷቸዋል።

የቀድሞ የሶቭየት ህብረት ትልልቅ ዝግጅቶችንም በመምራትም ይታወቃሉ ለምሳሌም ያህል የሞስኮ የሬድ ስኩዌር ሰልፎችና የኮሚኒስት ጉባዔዎችም ተጠቃሽ ናቸው።

የ15 አገራት ጥምረት የሆነችው የሶቭየት ህብረት መሪዎችም ሲሞቱም በክሬምሊን መካነ መቃብር የሚደረገው የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ማብራሪያዎችንና የሃዘን መግለጫዎችንም ያነቡ ነበር።

ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ መገባደጃ ላይ የቴሌቪዥን ዜና ሁኔታ በአለም ዙሪያ እየተቀየረ ነበር። ዜና አንባቢዎች አስተዋዋቂዎች ብቻ ሳይሆን ሙያ ያላቸው ጋዜጠኞች መሆን ጀመሩ።

በሶቪየት ኅብረትም የሆነው ተመሳሳይ ነበር እናም ኢጎር ኪሪሎቭ ከቴሌቪዥን እይታ መጥፋት ጀመሩ።

በወቅቱም ስለተፈጠረው ሁኔታ ኢጎር ሲናገሩ "በሚዲያው ላይ የተከሰተው ጥፋት ነው" ብለዋል።

አዳዲሶቹ የቴሌቪዥን አቅራቢዎች በጥድፊያ የተሞሉና የሩሲያን ህዝብ ፍላጎትም ያልተረዱ ናቸው በማለትም "ሩሲያውያን በፍጥነት ማውራት አይወዱም" ማለታቸውም ተገልጿል።

ታላቋ የሶቭየት ህብረት በአውሮፖውያኑ 1991 ፈራርሷ ወደተለያዩ አገሮች መበታተኗ ይታወቃል።