የቡድን 20 መሪዎች ታሪካዊ የተባለ የግብር ስምምነት ላይ ደረሱ

የቡድን 20 መሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የዓለማችን 20 ዋና ታላላቅ የኢኮኖሚ መሪዎች የግዙፍ ኩባንያዎች ትርፍ ላይ ቢያንስ 15 በመቶ ግብር የሚጣልበትን ዓለም አቀፍ ስምምነት አጽድቀዋል።

በርካታ አለም አቀፍ ኩባንያዎች ትርፋቸውን ለማጋበስ ሲሉ ዝቅተኛ የግብር ክፍያ ባለባቸው ስፍራዎች እያስመዘገቡ ነው የሚለውን ስጋት ተከትሎ ነው ይህ ውሳኔ ያለፈው።

ስምምነቱ የጸደቀው በሮም በተካሄደው የቡድን 20 መሪዎች በሙሉ ድምፅ ነው።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ መሪዎቹ በአካል ተገኝተው ባደረጉት የመጀመሪያ ስብሰባ የአየር ንብረት ለውጥና ኮቪድ-19 ሌሎቹ አጀንዳዎችም ሆነው ተነስተዋል።

ከ19 ሀገራት እና ከአውሮፓ ህብረት የተውጣጣው የቡድን 20 አባላት መሪዎች ሁሉም በሚባል ሁኔታ በአካል ቢገኙም የቻይናው ዢ ጂንፒንግ እና የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን የተሳተፉት በቪዲዮ አማካኝነት ነው።

የግብር ስምምነቱን ያቀረበችው አሜሪካ ስትሆን በዛሬው ዕለትም በይፋ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በአውሮፓውያኑ 2023ም ተግባራዊ እንደሚሆንም ዘገባው አክሎ አትቷል።

የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ጃኔት የለን እንዳሉት ታሪካዊው ስምምነቱ ለዓለም አቀፉ ምጣኔ ኃብት "ወሳኝ ጊዜ" ነው እናም "በኩባንያዎች ግብር ላይ ያለውን ጎጂ እሽቅድምድም እንዲያከትም ያደርገዋል" ብለዋል ።

በአሜሪካ ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ተጨማሪ ቀረጥ መክፈል ቢኖርባቸውም የአሜሪካ ቢዝነሶች እና ሰራተኞች ከስምምነቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ሚኒስትሯ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

የቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ በጉጉት ሲጠበቅ ከነበረው በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ከሚመክረው ኮፕ26 (COP26 ) በፊት ተካሂዷል።

ይህ በግላስጎው የሚደረገው ስብሰባ የፊታችን ሰኞ የሚጀምር ሲሆን በቡድን 20 የተደረገው ጉባዔ ውሳኔዎች ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳርፍበትም ተጠቁሟል።