ሩስያዊው ተዋናይ ከመድረክ ላይ ወድቆ ሞተ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩስያዊው ተዋናይ ሞስኮ ከሚገኘው ታዋቂው ቦልሾይ ትያትር ወድቂ ሕይወቱ ማለፉ ተሰምቷል።
ቲያትር ቤቱ እንዳለው ዬቭጌኒ ኩሌሽ የሞተው ሳድኮ የተሰኘ የኦፔራ ትዕይንት እየታየ ሳለ መቼት ሲቀየር በተፈጠረ አደጋ ምክንያት ነው።
አብረውት ይሠሩ የነበሩ ተዋንያን በድንጋጤ ሲሯሯጡ የሚያሳይ ምስል ማሕበራዊ ድር አምባ ላይ ታይቷል። የተዋናዩን ሕይወት ለማትረፍ ብዙዎች ሙከራ ቢያደርጉም ሳያሳካለቸው ቀርቷል።
መርማሪዎች የ37 ዓመቱ ትያትረኛ በምን ምክንያት ሊሞት እንደቻለ ምርመራ እያደረጉ እንዳለ ይፋ አድርገዋል።
ቅዳሜ አመሻሹን መግለጫ የለቀቀው ቦልሾይ ትያትር ቤት "አደጋው እንደተፈጠረ ነው ትዕይንቱ እንዲቆም የተደረገው። ተመልካቹም ወዲያው ወደ ቤቱ እንዲመለስ አድርገናል" ብሏል።
ተዋናዩ ኩሌሽ መድረኩ እየተቀየረ ሳለ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ሄዶ ነው ሊወድቅ የቻለው እየተባለ ነው።
በአደጋው የደነገጡ ተመልካቾች መጀመሪያ ሁኔታው የትዕይንቱ አካል መስሎን ነበር ሲሉ በማሕበራዊ ድር አምባ ገፆቻቸው ፅፈዋል።
ነገር ግን ሌሎች ተዋናዮች በሁኔታው ተደናግጠው መሯሯጥ ሲጀምሩ ነው አብዛኛው ተመልካች ነገሩ አደጋ መሆኑ የገባው።
ተመልካቾች እንደሚሉት "ሰዎች አምቡላንስ ጥሩ"፤ "ደም ይታየናል" ማለት ሲጀምሩ ነው አብዛኛው ታዳሚ ግራ የተጋባው።
የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ተዋናዩ ከፈረንጆቹ 2002 ጀምሮ በትያትር ቤቱ ሲያገለግል ቆይቷል።
ከዓለማችን ታዋቂ ትያትር ቤቶች አንዱ በሆነው የሞስኮው ቦልሾይ አደጋ ሲያጋጥም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ከስምንት ዓመታት በፊት አንድ ነባር የቫዮሊን ተጫዋች እንዲሁም ከመድረክ ወድቆ ሕይወቱ አልፎ ነበር።
ቫዮሊን ተጫዋቹ ቪክቶር ሴዶቭ በትያትር ቤቱ ለአራት አሥርት ዓመታት አገልግሏል።












